በቦሌ አየርመንገድ አካባቢ የተከሰተው የእሳት አደጋ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር መዋሉን ኮሚሽኑ ገለጸ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋው የተከሰተው ከአውሮፕላን ማረፊያው ቅጥር ውጭ መሆኑን ገልጾ በቃጠሎው ምክንያት ምንም አይነት በረራ አለመስተጓጎሉን አስታውቋል
በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ የተከሰተው የእሳት አደጋ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር መዋሉን ኮሚሽኑ ገለጸ።
የአዲስ አበባ እሳት እና አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን ለአል ዐይን አማርኛ እንደገለጹት፥ የእሳት አደጋው ቦሌ ወረዳ 1 ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ከቀኑ 9፡41 ላይ በመኖርያ ቤቶች ላይ የተፈጠረ ነው።
የአደጋው መንስኤ እየተጣራ ነው ያሉት የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ አደጋው በአየር መንገዱ ውስጥ እንደተከሰተ የሚወራው ወሬ ሀሰት ነው ብለዋል፡፡
እስካሁን ባለው በአንድ የእሳት አደጋ ሰራተኛ ላይ ከደረሰ አደጋ በስተቀር በሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት አለመድረሱን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ተናግረዋል።
በቀጣይ የአደጋው መንስኤ እና ያስከተለው ሙሉ ጉዳት ተጣርቶ ይፋ ይደረጋልም ብለዋል ባለሙያው።
የኢትጵያ አየር መንገድ በበኩሉ በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ አደጋው የተከሰተው ከአውሮፕላን ማረፊያው ቅጥር ውጭ መሆኑን ገልጾ፣ በቃጠሎው ምክንያት ምንም አይነት በረራ አለመስተጓጎሉን አስታውቋል።