ውሳኔው እስካሁን ያልተገታውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመቆጣጠር ያለመ ነው ተብሏል
ውሳኔው እስካሁን ያልተገታውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመቆጣጠር ያለመ ነው ተብሏል
የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ህንድ ለ21 ቀናት ዜጎቿ እና ነዋሪዎቿ በቤታቸው እንዲቆዩ ያሳለፈችው ውሳኔ ዛሬ የሚጠናቀቅ ቢሆንም የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በቤት የመቆየቱ ግዴታ ለተጨማሪ 19 ቀናት እንዲራዘም ወስነዋል፡፡
ውሳኔው እስካሁን ያልተገታውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመቆጣጠር ያለመ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስረትጭቱን መግታት የቻሉ አንዳንድ ግዛቶች ግን ዋና ዋና ተግባራትን ማከናወን እንዲጀምሩ ሊፈቀድላቸው ይችላል ብለዋል፡፡
በተለይም ቫይረሱ ያልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ደህንነታቸው እንደተጠበቀ ማቆየት እጅግ አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ “በምንም አይነት ሁኔታ ቫይረሱ ወደ አዳዲስ አካባቢዎች እንዲሰራጭ ልንፈቅድ እንደማይገባ ለመላው ህዝቤ መልእክት አስተላልፋለሁ” ሲሉ ሞዲ በቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር ወቅት ህዝባቸውን ተማጽነዋል፡፡
“እስከ ሚያዝያ 25 ሁላችንም በቤት መቆየት አለብን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ህዝባቸው ባለፉት 21 ቀናት ያሳየውን ስነ-ምግባር በቀጣዮቹ ቀናትም እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
የሞዲን መግለጫ ተከትሎ የሀገሪቱ ሲቪል አቪዬሽን እስከ ሚያዝያ 25 ድረስ ሁሉም ዓለም አቀፍ እና የሀገሩስጥ በረራዎች እንደተቋረጡ ይቀጥላሉ ብሏል፡፡ የህንድ ምድር ባቡር ሚኒስቴርም አዋጁ እስከሚያበቃበት ቀን አገልግሎት እንደማይሰጥ ገልጿል፡፡
የእስካሁኑ እገዳ በሀገሪቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ አስከትሏል፡፡ አሁን ደግሞ መንግስት እገዳውን ማራዘሙ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ እንዳይፈታተነው ተሰግቷል፡፡
ከ 1.3 ቢሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ሀገሪቱ እስካሁን 10,363 የቫይረሱ ተጠቂዎች የተገኙባት ሲሆን 339 ሞት አስተናግዳለች ሲኤንኤን እንደዘገበው፡፡