በሕንድ ከነሐሴ አጋማሽ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ዝቅተኛ ዕለታዊ የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር ተመዘገበ
ከአሜሪካ በመቀጠል ሕንድ በተጠቂዎች ቁጥር በዓለም 2ኛ ደረጃ ላይ ነች
ሀገሪቱ በትናንትናው ዕለት 55,342 አዲስ ተጠቂዎችን ስትለይ 706 ሞት አስመዝግባለች
በሕንድ ከነሐሴ አጋማሽ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ዝቅተኛ ዕለታዊ የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር ተመዘገበ
ሕንድ በትናንትናው ዕለት 55,342 የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎችን ያስመዘገበች ሲሆን ይህም ቫይረሱ በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተባት በሚገኘው ህንድ ካለፉት 2 ወራት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ዝቅተኛው ቁጥር ነው፡፡
የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው እስካሁን ቫይረሱ የተገኘባቸው ዜጎች ቁጥር ከ7.17 ሚሊዮን በልጧል፡፡ ይሁንና የተጠቂዎች ቁጥር በመቀነስ ላይ እንደሚገኝ ሚኒስቴሩ ይፋ አድርጓል፡፡
ትናንት በ24 ሰዓታት ውስጥ 706 ሞት የተመዘገበ ሲሆን በሕንድ ቫይረሱ ህይወታቸውን የነጠቃቸው ሰዎች ቁጥር 109,856 ደርሷል፡፡
በጤና ሚኒስቴር መረጃ መሠረት ከመስከረም 9 እስከ 15 ባሉት ጊዜያት አማካይ ዕለታዊ የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር 92,830 ነበር ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ባሉት ጊዜያት ደግሞ አማካይ ቁጥሩ ቀንሷል፡፡ ባለፈው ሳምንት ውስጥ በየቀኑ የሚለዩ ተጠቂዎች አማካይ ቁጥርም ከ 73,000 በታች ወርዷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሕንድ በየቀኑ የምታደርገው የኮሮና ምርመራ ቁጥር 1.1 ሚሊዮን ገደማ እንደሆነ በአል አረቢያ ዘገባ ተገልጿል፡፡
ወደ 1.4 ቢሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ያላት ሕንድ ከ 7.8 ሚሊዮን በላይ ተጠቂዎችን ከተገኙባት አሜሪካ ብቻ ዝቅ ብላ በተጠቂዎች ቁጥር ከዓለም ሁለተኛ ነች፡፡