“ከሰማይ ወረደ” በተባለ እሳት በደቡብ ክልል ከምባታ ጠምባሮ ዞን 30 ቤቶች ተቃጠሉ፡፡
“ከሰማይ ወረደ” በተባለ እሳት በደቡብ ክልል ከምባታ ጠምባሮ ዞን 30 ቤቶች ተቃጠሉ፡፡
በከምባታ ጠምባሮ ዞን ከጥቂት ቀናት በፊት ጥር 29 ቀን 2012 ዓ.ም ዓርብ ለሊት አግራሞትን የሚያጭር ክስተት መፈጠሩ ተሰምቷል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች “ከሰማይ ወረደ”ያሉት እሳት በዞኑ ጠምባሮ ወረዳ ዱርጊ፣ ሲገዞ፣ ለዘንባራ እና ሆዶ በተባሉ በአራት ቀበሌያት ውስጥ 30 የሳር ቤቶችን ማቃጠሉን የከምባታ ጠምባሮ ዞን ህዝብ ግንኙነት ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡
የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ዘላለም ደስታ ለአል-ዐይን እንደገለጹት እሳቱ በአራቱም ቀበሌያት ዓርብ ለቅዳሜ አጥቢያ ከሌሊቱ 7፡00 ጀምሮ በተመሳሳይ ሰዓት ተከስቶ ነው ከየቀበሌው በድምሩ 30 ቤቶችን ያቃጠለው፡፡
ከቤቶቹ በተጨማሪ ጎን ለጎን ካሉ ሁለት የጤፍ ክምሮች አንዱን ሲያቃጥል ስድስት የዳልጋ ከብቶችም የአደጋው ሰለባ ሆነዋል፡፡
ከተቃጠሉት ሳር ቤቶች አጠገብ ያሉ ባለቆርቆሮ ክዳን ቤቶች አልተነኩም ያሉት አቶ ዘላለም በሰው ላይም ጉዳት አልደረሰም ብለዋል፡፡
ስለክስተቱ መረጃ እንደደረሳቸው እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች የዞኑ ባለስልጣናት ወደ ስፍራው ሄደው ባደረጉት ማጣራት ያገኙት መረጃ ግራ እንዳጋባቸውም አቶ ዘላለም ተናግረዋል፡፡
እሳቱ በተከሰተ ወቅት የአካባቢው ኅብረተሰብ እሳቱን በዉሀ ለማጥፋት ሙከራ ሲያደርግ ዉሀው ይበልጥ እንዳባባሰው ተነግሮናል ሲሉም ኃላፊው ለአል-ዐይን በስልክ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም፣ ከሶስት ዓመታት በፊት፣ የጠምባሮ ወረዳ አጎራባች በሆነ የሀዲያ ዞን ምእራብ ሶሮ ወረዳ መሰል ክስተት መከሰቱን የገለጹት አቶ ዘላለም፣ የአካባቢው ኅብረተሰብ በወቅቱ እሳቱን በእልልታ ማጥፋቱን በማስታወስ የአሁኑን እሳትም በዚሁ መንገድ ማጥፋታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እንደተናገሩም ጠቁመዋል፡፡
እሳቱ ከሰማይ ከመውረዱ ውጭ፣ በአካባቢው የእሳት ቃጠሎ የሚያስነሳ ግጭትም ይሁን ሌላ ምንም ምክኒያት እንደሌለም የአካባቢው ኅብረተሰብ አባላት ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በኅብረተሰቡ ዘንድ ክስተቱ የፈጣሪ ቁጣ ውጤት ነው የሚል እምነት ያሳደረ ሲሆን ለበደላችን ንስሀ በመግባት ከፈጣሪ ጋር መታረቅ አለብን በማለት ኅብረተሰቡ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡
እንደ አቶ ዘላለም ደስታ ትዝብትም ቢሆን የእሳቱ ክስተት ከወንጀል ጋር ይያያዛል ለማለት ይከብዳል፡፡ የጎሳ ጸብ ውጤት ነው እንኳን እንዳይባል በአካባቢው ጎሳዎች መካከል ቅራኔ አለመኖሩን እንዲሁም የተቃጠሉት ቤቶችም ከተለያዩ የጎሳ አባላት፣ ከዚያም ሲያልፍ የሳር ቤቶች ብቻ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ፖሊስ የእሳቱን መንስኤ እና የጉዳቱን መጠን በተመለከተ ተጨማሪ የማጣራት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ የከምባታ ጠምባሮ ዞን ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር አብረሃም ቲርካሶ ለዞኑ አስተዳደር ገልፀዋል።
እስካሁን ግን ከእሳቱ ቃጠሎ ጋር በተያያዘ ፖሊስ ምንም አይነት የወንጀል መረጃ አላገኘም፡፡