ከዛሬ ጀምሮ የጦር መሳሪያ ማስመዝገብና ማሳወቅ ግደታ እንደሆነ ተገልጿል
በአዲስ አበባ ከተማ ከዛሬ ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ሁለት ቀናት ማንኛውም ግለሰብ በእጁ የሚገኝን ጦር መሳሪያ የማስመዝገብ እና የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበት ተገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የሠላምና ፀጥታ አስተዳር ቢሮ ኃላፊ ቀነዓ ያደታ ( ዶ/ር) በከተማዋ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫው ከዚህ ቀደም ያስመዘገበም ሆነ ያላስመዘገበ ማንኛውም ግለሰብ በእጁ የሚገኘውን የጦር መሳሪያ በአዲስ መልክ የማስመዝገብ እና የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበት ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሰረት ከዛሬ ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ሁለት ቀናት ማንኛውም ግለሰብ በአካባቢው ወዳለ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ ማስመዝገብ እንዳለበት የገለጹት ዶ/ር ቀነዓ ይህ የሚደረገውም የከተማዋን ሰላም የበለጠ ለማረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡
ህወሓት ይዟቸው በነበረው በአፋርና አማራ ክልል አካባቢዎች ከ480 በላይ ንጹሃንን ገድሏል- ፍትህ ሚኒስቴር
በከተማዋ የሀሰት ወሬ ውዥንብሮች እንዳሉ ያነሱት ኃላፊው ይህ ውዥንብር ቢኖርም የአዲስ አበባ፣ የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሰራዊት ከኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ካሉ ሰላምና ደህንነት አባላት ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የሠላምና ፀጥታ አስተዳር ቢሮ ኃላፊ ሕብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመከላከያ ሰራዊቱና በሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ላይ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በማሰራጨት ላይ የሚሳተፉ አካላት ላይ መንግስት እርምጃ እንደሚወስድም ኃላፊው አስጠንቅቀዋል።
በቀጣይ ቀናትም የአዲስ አበባን ሰላም ለማስከበር በተለያዩ ቤቶች እና የንግድ ቦታዎች ፍተሻ እንደሚደረግባቸው የገለጹት ሃላፊው ለዚህም ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።