ህወሓት ይዟቸው በነበረው በአፋርና አማራ ክልል አካባቢዎች ከ480 በላይ ንጹሃንን ገድሏል- ፍትህ ሚኒስቴር
109 የአስገድዶ መድፈር ኢሰብዓዊ ድርጊቶች መፈጸማቸውንም ሚኒስቴሩ በሪፖርቱ ጠቅሷል
ምርመራው በአፋርና በአማራ ክልል በሚገኙ በህወሃት ተይዘው በነበሩና ኋላ ላይ ነጻ በወጡ አካባቢዎች ላይ ነው የተካሄደው
በአማራ ክልል በሰሜን እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች እንዲሁም በአፋር ክልል በሚገኙ ወረዳዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ወንጀል ምርመራን እና የመጀመሪያ ደረጃ ግኝቶችን አስመልክቶ የፍትህ ሚኒስቴር መግለጫ ሰጥቷል።
ምርመራው የተካሄደው በአፋር እና በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በሚገኙ በህወሃት ተይዘው በነበሩ እና ኋላ ላይ በሕግ ማስከበሩ ዘመቻው ነጻ በወጡ አካባቢዎች ላይ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
በውጤት ደረጃም ህወሓት በሰሜን ጎንደር ዞን ለጊዜው በዝርዝር ማስረጃ የተለዩ የ96 ሰዎች ሞት፣ 53 የአካል ጉዳት፣ 29 አስገድዶ መደፈር፣ 11 ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ፣ 6 እገታ እንዲሁም የመንግስት፣ የግል እና የሀይማኖት የተለያዩ ተቋማት ንብረቶች ላይ መጠነ ሰፊ ዘረፋና ውደመት መፈጸሙን አረጋግጫለሁ ብሏል።
በደቡብ ጎንደር ዞን ባሉ አምስት ወረዳዎች ደግሞ በድምሩ የ129 ሰዎች ሞት፣ የ54 ሰዎች የአካል ጉዳት፣ በንፋስ መውጫ ከተማ ብቻ የ73 ሴቶች የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እንዲሁም በርካታ ግለሰቦች ንብረት ላይ ውድመት መድረሱን ሪፖርቱ አመላክቷል።
በአፋር ክልል ነሃሴ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በጋሊኮማ ቀበሌ መጠለያ ጣቢያ ላይ በተፈጸመ ጥቃት የ240 ሰዎች ሞት፣ 42 ሰዎች የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፤ በቀሪዎቹ ሶስት ወረዳዎች ደግሞ የ17 ሰዎች ሞት እና ለ17 ሰዎች የአካል ጉዳት እንዲሁም 7 ሴቶች የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች እንደተፈጸመባቸው መረጋገጡን ሪፖርቱ አመላክቷል።
በሁለቱም ክልሎች ከሰላማዊ ዜጎች ንብረት በተጨማሪ በመንግስት እና በግል ተቋማት ላይ ማለትም ት/ቤቶች፣ ጤና ኬላዎች፣ የህብረት ስራ ማህበራት እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት፣ በመስጊዶች እና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ላይ የዘረፋ እና ውድመት ድርጊቶች በስፋት መፈጸማቸውን አስታውቋል።
በአጠቃላይ ምርመራው በሂደት ላይ ያለ ከመሆኑ አንጻር እስከ አሁን በተደረሰበት ብቻ በሁለቱም ክልሎች በተፈጸሙት የወንጀል ድርጊቶች 482 ሞት፣ 165 የአካል ጉዳት እና 109 የአስገድዶ መድፈር ኢሰብዓዊ ድርጊቶች መፈጸማቻን በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በአካባዎቹ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰላማዊ ዜጋ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል ያለው ሪፖርቱ፤ ለአብነትም በአፋር ክልል 112 ሺህ 158 ዜጎች፣ በሰሜን ጎንደር 135 ሺህ 310 ዜጎች እንዲሁም በደቡብ ጎንደር ከ 470 ሺህ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውንም አስታውቋል።
በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል የተፈጠረው ግጭት አንድ አመት ያስቆጠረ ሲሆን መንግስት ከአራት ወራት በፊት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ከትግራይ ክልል ቢወጣም ጦርነቱ ሊቆም አልቻለም፡፡ ህወሃት ወደ አጎራባች ክልሎች በተለይም ወደ አማራ ክልል ውስጥ በመግባት እስካሁን ብዙ ቦታዎቸን ይዟል፡፡
ህወሃት በያዛቸው አካባቢዎች እስካሁን ሴቶች እየተደፈሩና ንጹሃን እየተገደሉ መሆናቸውን ነዋሪዎች ሲገልጹ ቆይዋል፡፡
መንግስት ህወሓትን በተወካዮች ም/ቤት በአሸባሪነት ያስፈረጀ ሲሆን መከላከያና የክልል የጸጥታ ሃይሎች በህወሓት ላይ እርምጃ እንዲወሰዱ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡