ፖለቲካ
አሜሪካ፤ ህወሓት ወደ ደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች መቃረቡን እንዲገታ ጥሪ አቀረበች
ተኩስ ለማቆም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ድርድር ይጀመርም ነው ዋሽንግተን ያለችው
ዋሽንግተን ህወሓት ከአማራ እና አፋር ክልሎች ይውጣ ስትልም በድጋሚ ጥሪ አቅርባለች
የጦርነቱ መዛመት እጅግ አሳስቦኛል ያለችው አሜሪካ ህወሓት፤ ከአማራ እና አፋር ክልሎች እንዲወጣ በድጋሚ ጥሪ አቀረበች።
ህወሓት ወደ ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች መቃረቡን እንዲገታም ጥሪ ያቀረበችው አሜሪካ ከባድ መሳሪያዎችን ወደ ከተሞች እንዳይተኩስ አሳስባለች።
መንግስት በመቀሌና በሌሎች የትግራይ አካባቢዎች የፈፀማቸውን የአየር ድብደባዎች በጽኑ መቃወሜ ይታወስልኝ ያለችው ዋሽንግተን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቷ በኩል ባወጣችው መግለጫ ሁሉም አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ድርድር መጀመር አለባቸው ብላለች።
በትግራይም ይሁን በአማራ ወይም በአፋር ሰብዓዊ ድጋፎችን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗንም አስታውቃለች።
ሰብዓዊ ድጋፎች አይቆራረጡ ስትል ጥሪ ያቀረበችም ሲሆን የሲቪል ደህንነት እንዲጠበቅ፣ መብቶች እንዲከበሩና አጥፊዎች እንዲጠየቁም ጠይቃለች።