እንግሊዝ የአለም ዋንጫውን ታነሳለች ብሎ 18 ሺህ ቲሸርቶችን ያሳተመው ግለሰብ ኪሳራ ገጥሞታል
ሶስቱ አናብስት በሰማያዊዮቹ ሲሸነፉ ሀዘኑ የተደራረበበት እንግሊዛዊ የቲሸርቱን ዋጋ በሶስት እጅ ቀንሷል
“በኩራት ለበሳችሁትም የመስኮት መወለወያ አደረጋችሁት” ግዙኝ የሚል ተማጽኖውንም እያሰማ ነው
እንግሊዛዊው የእግር ኳስ አፍቃሪ ግምቶችን ሁሉ ከንቱ ባደረገው የአለም ዋንጫ ተጎጂ ሆኗል።
ካርል ባክስተር የተባለው ግለሰብ ሀገሩ በኳታር እንደምትነግስ ምንም አይነት ጥርጣሬ አልነበረውም።
ሶስቱ አናብስት የአለም ዋንጫውን ከዶሃ ወደ ለንደን ይዘው እንደሚመለሱም ሙሉ እምነት ነበረው።
ከሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች አስቀድሞም “እንግሊዝ የ2022 የአለም ዋንጫ ሻምፒዮን በመጨረሻም ዋንጫው ቤታችን ገብቷል’’ የሚል ጽሁፍ ያለባቸውን 18 ሺህ ቲሸርቶች አትሞ የሚያገኘውን ትርፍ ያሰላ ጀመር።
በ1966 በዌንብሌይ ስታዲየም ራሷ ያዘጋጀችውን የአለም ዋንጫ ካነሳች በኋላ የአለም ዋንጫው እንደናፈቃት የቀረችው እንግሊዝ ግን እንኳን ዋንጫውን ልታነሳ ለግማሽ ፍጻሜው አልደረሰችም።
በሩብ ፍጻሜው ፍልሚያ በፈረንሳይ 2 ለ 1 ተረታ ከዶሃ ተሰናብታለች።
ይህን ጨዋታ ከየትኛውም እንግሊዛዊ በተለየ ስሜት የተከታተለው ባክስተር ሃዘኑ ተደራርቦበታል።
“ለአመታት ምንም አይነት ጽሁፍ የሌላቸውን ቲሸርቶች ገዝተን ምንም አልተፈጠረም (ዋንጫ ወስደን ያሻንን አልጻፍንባቸውም)፤ እናም ድልን የሚተነብይ ጽሁፍ ያላቸው ቲሸርቶች አሳተምኩ” ይላል የ46 አመቱ ባክስተር።
ሶስቱ አናብስት ባሳዩት ብቃት እንደሚኮራ የሚያነሳው ነጋዴ፥ ለእንግሊዛውያን መልዕክት አለው፤ የታተሙትን 18 ቲሸርቶች ግዙኝና ከኪሳራ ታደጉኝ የሚል።
“የቲሸርቶቹን ዋጋ ቀንሰናል፤ በኩራት ልበሷቸው፣ ለታሪክ በክብር አስቀምጧቸው፣ የመስኮት መወልወያም ልታደርጓቸው ትችላላችሁ፣ አላውቅም” የሚል የግዙኝ ተማጽኖውንም በድረገጹ ላይ አስፍሯል።
የሶስት ልጆች አባቱ የእግር ኳስ አፍቃሪ ነጋዴ ለቲሸርቶቹ ዝግጅት ያወጣው ወጪ የተጋነነ አይደለም፥ የተወሰኑትንም ሽጧል ተብሏል።
እንግሊዝ በወንዶቹ ባይሳካላትም በሴቶቹ የ2022 የአውሮፓ ዋንጫን ስላነሳች የቲሸርቱን ሽያጭ ወዳዚያው የማዞር አማራጭም ይዟል።
29 ነጥብ 99 ፓውንድ ስተርሊንግ ሊሸጥ የነበረው ነጭ ቲሸርት አሁን የ9 ነጥብ 99 ፓውንድ ዋጋ ወጥቶለታል መባሉን ስካይ ኒውስ አስነብቧል።