የኒጀር ወታደራዊ ጁንታ ሶስት ከፍተኛ ፖለቲከኞችን አሰረ
የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ጥምረት የሆነው ኢኮዋስም ወታደራዊ ጁንታው ባዙምን ወደ ቦታቸው እንዲመልስ አስጠንቅቋል
መፈንቅለ መንግስት በማድረግ ስልጣን የያዘው የኒጀር ወታደራዊ ጁንታ ከስልጣን የተወገደው መንግስት አባል የሆኑ ሶስት ተጨማሪ ከፍተኛ ፖለቲከኞችን አስሯል
የኒጀር ወታደራዊ ጁንታ ሶስት ከፍተኛ ፖለቲከኞችን አሰረ።
መፈንቅለ መንግስት በማድረግ ስልጣን የያዘው የኒጀር ወታደራዊ ጁንታ ከስልጣን የወገደው መንግስት አባል የሆኑ ሶስት ተጨማሪ ከፍተኛ ፖለቲከኞችን መታሰራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
በኒጀር ዲሞክራሲያዊ ስርአቱ ወደ ነበረበት እንዲመለስ እየደረገ ያለውን አለምአቀፍ ጥሪ ወደ ጎን የተወው ስልጣን የተቆጣጠረው ወታደር ማሰሩን መቀጠሉ ተገልጿል።
የአፍሪካ ህብረት፣ ተመድ ፣ የአውሮፖ ህብረት እና ሌሎች ኃይሎች ወታደራዊ ጁንታው በተመረጡት የኒጀር መሪ ሞሀመድ ባዙም ላይ የፈጸሙትን መፈንቅለ መንግስት አውግዘዋል።
ይህ መፈንቅለ መንግስት ከሶስት አመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በማዕከላዊ እና ምዕራብ አፍሪካ የተፈጸመ ሰባተተኛው መፈንቅለ መንግስት ነው።
በኒጀር የተፈጠረው ችግር የሳህል ቀጣናን ወደ አለመረጋጋት የከተዋል የሚል ስጋትም ፈጥሯል።
አሜሪካ፣ የቀድሞ የኒጀር ቅኝ ገዥ ፈረንሳይ እና ሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት በኒጀር ጦር ያላቸው ሲሆን ከኒጀር መንግስት ጋር በመተባበር ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት አላቸው የሚሏቸውን ኃይሎች ሲዋጉ ቆይተዋል።
አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን ሀገራት ለኘሬዝደንት ባዙም ድጋፋቸውን እያሳዩ ነው፣ ከተፈጸመባቸው እገታም እንዲለቀቁ እየጠየቁ ይገኛሉ።
የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ጥምረት የሆነው ኢኮዋስም ወታደራዊ ጁንታው ባዙም ወደ ቦታቸው እንዲመልስ አስጠንቅቋል። ፕሬዝዳንቱን ወደ ስልጣናቸው የማይመልስ ከሆነ ኢኮዋስ ወደ ኒጀር ጦር ሊልክ እንደሚችልም ማስጠንቀቁ ይታወሳል።
ነገርግን ወታደራዊ ጁንታው የኢኮዋስ ጦር የመላክ እቅድ ደም የሚያፋስስ ነው ሲል ተቃውሟል።