የኡጋንዳ መንግስት አፍጋናውያንን መቀበል ቢጀምርም፤ የራሱን ዜጎች ከአፍጋኒስታን ማስወጣት አልቻለም
ኡጋንዳ አፍጋናውያን ስደተኞችን በጊዜያዊነት መቀበል መጀመሯን በዛሬው እለት አስታውቃለች።
የመጀመሪያው ዙር አፍጋናውያን ስደተኞች በዛሬው እለት ኡጋንዳ ካምፓላ መድረሳቸውንም ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
ካምፓላ አፍጋናውያን ስደተኞችን መቀበል ጀመረችው በአሜሪካ ጥያቄ ሲሆን፤ የኡጋንዳ መንግስትም በስጋት ውስጥ የሚገኙ ስደተኞችን በጊዜያዊነት ተቀብሎ ለማስተናገድ መስማማቱን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በጊዜያዊነት ወደ ኡጋንዳ የሚገቡት ስደተኞችም ከቆይታ በኋላ ወደ አሜሪካ እና ሌሎች የዓለም ሀገራት መዳረሻዎች የሚያቀኑ መሆኑም ታውቋል።
በዚህም መሰረት ኡጋንዳ ለመቀበል ከተስማማችው 2 ሺህ አፍጋናዉያን ስደተኞች መካከል በቻርተርድ በረራ ከካቡል የተነሳው የመጀመሪያው የስደተኞች ቡድን ዛሬ ማለዳ ላይ ኢንቴቤ አውሮፕላን ማረፊያ ድርሷል።
ስደተኞች ኢንቴቤ አውሮፕላን መረፊያ ሲደርሱም አስፈላጊው የደህንነት ፍተሸ እና የኮቪድ 19 ምርመራዎች ተደርገውላቸው ወደ ሀገሪቱ መግባታቸውም ነው ተነገረው።
አፍጋናውያኑ ካምፓላ ቢደርሱም አፍጋኒስታን ውስጥ አሁንም ቢሆን መውጫ አጥተው የተቀመጡ ኡጋንዳውያን እንዳሉ የሀገሪቱ መንግስት አስታውቋል።
የኡጋንዳ መንግስት በአፍጋኒስታን የሚገኙ ኡጋንዳውያንን ለማስወጣት የአውሮፕላን በረራዎችን እንደሚያመቻች አስታውቋል።
የአሜሪካ እና የሌሎች የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሃገራት ጦር አፍጋኒስታንን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ የታሊባን ታጣቂ ቡድን ሃገሪቱን መቆጣጠሩ እና በርካታ አፍጋናውያን ለስደት መዳረጋቸው የሚታወቅ ነው።