ካምፓላ አፍጋናውያኑን የምትቀበለው በአሜሪካ ጥያቄ
ኡጋንዳ 2 ሺ ገደማ አፍጋናውያን ስደተኞችን በጊዜያዊነት ልትቀበል ነው፡፡
ካምፓላ አፍጋናውያኑን የምትቀበለው በአሜሪካ ጥያቄ ሲሆን ፕሬዝዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ጥያቄውን ተቀብለውታል፡፡
ለዚህም ከትናንት ጀምሮ አስፈላጊው ዝግጅት መደረግ መጀመሩን የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት እንዲሁም ስደተኞች ሚኒስትር ኢስተር አንያኩን ተናግረዋል፡፡
ስደተኞቹ አሜሪካ ወደ ሌላ ቦታ እስከምታዛውራቸው ድረስ በኡጋንዳ እንደሚቆዩም ነው ሚኒስትሯ የገለጹት፡፡
ወደ ኡጋንዳ እንደሚመጡ ከሚጠበቁት አፍጋናውያን መካከል 500 ያህሉ ትናንት ሰኞ ነሃሴ 10 ቀን 2013 ዓ/ም ከምስራቅ አፍሪካዊቷ ሃገር እንደሚደርሱ ቢጠበቅም አልመጡም፡፡
“ችግሩ ድንገተኛ መሆኑን ተከትሎ በየትኛውም ሰዓት ሊመጡ እንደሚችሉ እንጠብቃለን፡፡ በተለያዩ ዙሮች ሊመጡ የሚችሉ 2 ሺ ያህል ስደተኞችን ነው እንድንቀበል የተጠየቅነው” ብለዋል ኢስተር አንያኩን፡፡
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ የስደተኞቹ ወጪ በአሜሪካ መንግስት የሚሸፈን ነው፡፡
አምስት አምስት መቶ እየሆኑ ወደ ኡጋንዳ የሚመጡት ስደተኞቹ ለ3 ወራት ያህል እንደሚቆዩ ይጠበቃል፡፡
የአሜሪካ እና የሌሎች የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሃገራት ጦር አፍጋኒስታንን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ የታሊባን ታጣቂ ቡድን ሃገሪቱን መቆጣጠሩ እና በርካታ አፍጋናውያን ለስደት መዳረጋቸው የሚታወቅ ነው፡፡