ዩክሬን ለጀርመኑ የአውሮፓ ዋንጫ ማለፏን አረጋገጠች
የሰርሂ ሬብሮቭ ቡድን አይስላንድን በማሸነፍ በጦርነት ውስጥ ለሚገኙ ዩክሬናውያን ተስፋና ደስታን መፍጠር ችሏል
ኦሌክሳንደር ዚንቼንኮ “ለነጻነታችን ህይወታቸውን እየሰጡ ያሉ ዩክሬናውያንን ደም በመጋራቴ እኮራለሁ” ብሏል
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ጦርነት ከጀመረች ወዲህ ትልቁን የእግርኳስ ውጤት አስመዝግባለች።
የሀገሪቱ ብሄራዊ ቡድን አይስላንድን 2 ለ 1 በመርታት በሰኔ ወር በጀርመን ለሚካሄደው የአውሮፓ ዋንጫ ማለፉን አረጋግጧል።
አይስላንድ በመጀመሪያው አጋማሽ በአልበርት ጉድሙንድሰን ጎል ብትመራም ቪክቶር ሲጋንኮቭ እና የቼልሲው አጥቂ ሙድሪክ ያስቆጠሯቸው ጎሎች ዩክሬንን ለድል አብቅተዋል።
የሰርሂ ሬብሮቭ ቡድን በጀርመኑ የአውሮፓ ዋንጫ ቤልጂየም፣ ስሎቫኪያ እና ሮማኒያን ባካተተው ምድብ 5 ውስጥ ገብታለች።
አሰልጣኝ ሬብሮቭ አይስላንድን በማሸነፍ ወደ አውሮፓ ዋንጫው መግባት በጦርነት ውስጥ ለሚገኙት ዩክሬናውያን የተወሰነም ቢሆን ደስታ የሚፈጥር ነው ብለዋል።
የዩክሬን ብሄራዊ ቡድን አምበል ኦሌክሳንደር ዚንቼንኮም የምሽቱ ጨዋታ እጅግ ፈታኝና ስሜታዊ የሚያደርግ እንደነበር ነው የተናገረው።
“ለነጻነታችን ህይወታቸውን እየሰጡ ያሉ ዩክሬናውያንን ደም በመጋራቴ እኮራለሁ” ሲልም በሰላማዊው የውጊያ ሜዳ የተመዘገበው ስኬት እንዳስደሰተው ገልጿል።
የዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት የዩክሬን ብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎችን በሌሎች ሀገራት ሜዳዎች እንዲያደርግ አስገድዶታል።
የትናንቱ ከአይስላንድ ጋር የተደረገው ፍልሚያም በፖላንድ ዋርሳው መካሄዱ ይታወቃል።
የ2024 የአውሮፓ ዋንጫ ሰኔ 14 በሙኒኩ አሊያንዝ አሬና ጀርመን እና ስኮትላንድ በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀመራል። የፍጻሜው ጨዋታም ከአንድ ወር በኋላ በበርሊን ኦሎምፒያ ስታዲየም ይደረጋል።