ቪኒሺየስ ጁኒየር የዘረኝነት ጥቃት ከእግርኳስ የማገኘውን ደስታ እየነጠቀኝ ነው አለ
ብራዚላዊው አጥቂ በእያንዳንዱ ጨዋታ የሚደርስበትን የዘረኝነት ጥቃት መቋቋም ፈታኝ እንደሆነበት እምባ እየተናነቀው ተናግሯል
የሪያል ማድሪድ ተጫዋቹ ከስፔን ወጥቼ ዘረኞች የሚፈልጉትን እንዲያሳኩ ግን አልፈቅድላቸውም ብሏል
ብራዚል እና ስፔን በዛሬው እለት በሳንቲያጎ በርናባው የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋሉ።
ጨዋታው “አንድ ቆዳ” የሚል መፈክር ያለው ዘረኝነትን የመቃወም ዘመቻ አካል ነው ተብሏል።
ብራዚዊው ቪኒሺየስ ጁኒየር በዚህ ጨዋታ ዙሪያ መግለጫ ሲሰጥ በስፔን እየደረሰበት ያለው የዘረኝነት ጥቃት እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አለመሄድ አሳሳቢ ነው ብሏል።
“እግርኳስ መጫወት እፈልጋለሁ ግን ደግሞ ወደፊት እንዳትራመድ የሚያደርግ ነገር ይገጥምሃል፤ በዘረኝነት ስድብ ምክንያት ከእግርኳስ አገኝ የነበረውን ደስታ ተነጥቄያለሁ” ሲልም እምባና ሳግ እየተናነቀው ተናግሯል።
በእያንዳንዱ ጨዋታ የሚያስተናግደው ስድብና የጥላቻ ምልክት ከስፔን መውጣት እንዳለበት የሚያሳዩ ቢሆኑም በዚያው መቆየትን መምረጡንም ነው የገለጸው።
“በስፔን እቆያለው፤ ዘረኞችም ፊቴን ደጋግመው ያዩታል፤ ለሪያል ማድሪድ የምጫወት ደማቅ ተጫዋች ነኝ፤ ከቡድኔ ጋር ያሳካናቸው ዋንጫዎች ለበርካቶች ምቾት የማይሰጡ ናቸው” ያለው የ23 አመቱ አጥቂ፥ ከስፔን ወጥቼ ዘረኞች የሚፈልጉትን እንዲያሳኩ አልፈቅድላቸውም ብሏል።
ባለፈው አመት ብቻ ከዘረኝነት ጋር የተያያዙ10 ጥቃቶች የደረሱበት ቪኒሺየስ፥ “ላሊጋው የዘረኞች ነው” የሚል አስተያየት መስጠቱ ይታወሳል።
ባለፈው አመት ግንቦት ወር በቫሌንሽያ ደጋፊዎች የደረሰበት ጥቃትም ብራዚላዊው ተጫዋች አለማቀፍ ድጋፍ እንዲያገኝ እና ዘመቻ እንዲጀመር ማድረጉ አይዘነጋም።
ይሁን እንጂ በዚህ የውድድር አመትም በርካታ የዘረኝነት ጥቃቶች እንደደረሱበት የሚገልጸው የሪያል ማድሪዱ አጥቂ፥ ጥፋት በሚፈጽሙ ደጋፊዎች እና ተጫዋቾች ላይ የሚተላለፈው ቅጣት ዝቅተኛ መሆን ችግሩን እያስቀጠለው ነው ብሎ ያምናል።
“ቅጣቱን ከፍ በማድረግ አስተሳሰባቸውን (የዘረኝነት) መለወጥ ባይቻል እንኳን በስታዲየም፣ በካሜራ እይታ ውስጥ ሆነው መሳደብን መፍራት ይጀምራሉ” ሲልም ላሊጋው መፍትሄን ያበጅ ዘንድ ጠይቋል።
“በእግርኳስ ጨዋታ ቡድኔ ያሸንፍም ይሸነፍም እኔ ግን በሜዳ ውስጥ ተገኝቼ ዘረኞችን መታገሌ በራሱ ድል ነው” ሲልም በፈተና ውስጥ ለመጽናት መወሰኑን ሬውተርስ ዘግቧል።
ባለፈው አመት በተጫዋቹ ላይ የጥላቻ አርማ ይዘው የወጡ አራት ሰዎች 60 ሺህ ዩሮ እንዲከፍሉና ለሁለት አመት ስታዲየም ውስጥ እንዳይገኙ መወሰኑን የሚያነሳው የስፔን ላሊጋ በበኩሉ ለውጦች እንዳሉ ሲገልጽ ይደመጣል።