አምስት ኑክሌር የታጠቁ ሀገራት በኒው ዮርክ ስብሰባ ሊያደርጉ ነው
ከዩክሬን ጦርነት ወዲህ በሩሲያ እና በምዕራባዊያን መካከል ያለው ውጥረት እያየለ በመምጣቱ ስብሰባው አስፈላጊ ነው ተብሏል
በስብሰባ ኑክሌር የታጠቁት ሩሲያ፣አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ቻይና እና እንግሊዝ እንደሚሳተፉ ተገልጿል
አምስት ኑክሌር የታጠቁ ሀገራት በኒው ዮርክ ስብሰባ ሊያደርጉ ነው።
አምስት ኑክሌር የታጠቁ ሀገራት ቡድን በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ በአሜሪካ ኒው ዮርክ ስብሰባ ሊያደርጉ መሆኑን የሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ርያብኮቭ ተገልጿል።
በዚህ ስብሰባ ኑክሌር የታጠቁት እና የተመድ የጸጥታው ምክርቤት ቋሚ አባል የሆኑት ሩሲያ፣አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ቻይና እና እንግሊዝ እንደሚሳተፉ ሮይተርስ የሩሲያ መገናኛ ብዙሃንን ጠቅሶ ዘግቧል።
ርያብኮቭ ስብሰባው የሚካሄድበትን ቀን በትክክል አልጠቀሱም፤ ሀገራቱ በምን ኃላፊዎች ደረጃ እንደሚሳተፉም ግልጽ አላደረጉም። ከዩክሬን ጦርነት ወዲህ በሩሲያ እና በምዕራባዊያን መካከል ያለው ውጥረት እያየለ በመምጣቱ ስብሰባው አስፈላጊ ነው ተብሏል።
ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ የኑክሌር የጦር መሳሪያ አጠቃቀም ፖሊሲዋን መቀየሯን መናገራቸው ይታወሳል። ሞስኮ በአዲሱ የኑክሌር አጠቃቃም ፖሊሲዋ፣ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ልትጠቀም የምትችልባቸውን ሁኔታዎች ዘርዝራለች።
በጥር 2022 ሩሲያ በዩክሬን ላይ ልዩ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ ከመጀመሯ ከሳምንታት በፊት አምስቱ ኑክሌር የታጠቁ ሀገራት ኑክሌር በታጠቁ ሀገራት መካከል ጦርነት እንዳይኖር እንደሚሰሩ ገልጸው ነበር።
ሀገራቱ በወቅቱ "የኑክሌር ጦርነት አሸናፊ እንደሌለው እናረጋግጣለን፤ በፍጹም መጀመር የለበትም" ብለውም ነበር።
ሩሲያ በዩክሬን ያደረገችውን "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" የሚቃወሙት ምዕራባዊያን እስካሁን ድረስ ለዩክሬን የገንዘብ እና የጦር መሳሪያ ድጋፍ እያደረጉ ሲሆን በሩሲያ ላይ ደግሞ ማዕቀብ ከመጣል ጀምሮ የሚችሉትን ጫና ሁሉ እያሳደሩባት ነው።
ሩሲያ ምዕራባውያን ሀገራት ከመርዳት አልፈው በቀጥታ በጦርነቱ የሚሳተፉ ከሆነ ሶስተኛው የአለም ጦርነት ሊነሳ ይችላል ስትል አስፈራርታለች።