ከ6 ወር የጨቅላ እድሜ ጀምሮ የሚስተዋለውን የቅናት ስሜት እንዴት መቆጣጠር ይቻላል?
ቅናት ከሰው ሰው መጠኑ ቢለያይም በሁሉም ውስጥ የሚገኝ ሰውኛ ባህሪ እንደሆነ ይነገራል

ስሜቱ ከራስ አልፎ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት እንዳያበላሽ መቆጣጠር የምንችልባቸው 5 ዘዴዎች ምንድን ናቸው?
ሰዎች በተደጋጋሚ ከሚያንጸባርቋቸው ስሜቶች ወይም ባህሪዎች መካከል አንዱ እንደሆነ የሚጠቀሰው ቅናት በተለያዩ ሁኔታዎች እንዲሁም የህይወት አጋጣሚዎች የሚዳብር እና የሚገለጥ ነው፡፡
የስነልቦና እና ስነ ባህሪ ተመራማሪዎች ቅናትን በቁጣ ወይም ከሀዘን ስሜት መካከል የሚገኝ ሁለቱም ስሜቶች የሚንጸባረቁበት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
የአሜሪካ የስነልቦና መዝገበ ቃላት ቅናትን አሉታዊ ስሜት እንደሆነ ይገልጸዋል፤ ሌሎች ደግሞ ቅናት መጠኑ የማይበዛ ከሆነ የፍቅር ወይም የውዴታ መግለጫ እንደሆነ ያነሱታል፡፡
የሲኤንኤን የህክምና ጉዳዮች ዋና ዘጋቢ ዶክተር ሳንጃይ ጉብታ ቅናት መረጃዎችን የምንተረጉምበት እና የምንረዳበት መንገድ የሚፈጥረው ውጤት ነው ይላሉ፡፡
ቅናት ሙሉ ለሙሉ መጥፎ ስሜት እንዳልሆነ የሚናገሩት ሀኪሟ አንዳንድ ጊዜ አካባቢያችንን በጥርጣሬ እና በንቃት እንድንቃኝ የተሳሳተ ውሳኔ ከመወሰን እንደሚታደግ ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን ሰዎች ያለ በቂ መረጃ የተሰማቸውን ስሜት በመከተል ብቻ መጥፎ እርምጃ እንዲወስዱ ወይም የቀኑበት ሰው ስሜት ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ሊያደርጋቸው እንደሚችልም ነው የጠቆሙት፡፡
ከ6 ወር ጨቅላ ህጻን እድሜ ጀምሮ እንደሚስተዋል የሚነገርለት ቅናት የእኔ ብቻ ከሚል ስሜት፣ ካለመተማመን ፣ ሰዎች ከዚህ ቀደም ከገጠማቸው ልምድ አንዳንድ ግዜም በራስ ካለመተማመን ሊመነጭ ይችላል፡፡
የቅናት ስሜትን በተገቢው መንገድ ካልተያዘ የረጅም ጊዜ ግንኙነትን ሊያበላሽ፣ የፍቅር ወይም የትዳር ግንኙነትን ሊያፈርስ አለፍ ሲልም ነፍስ ሊያጣፋ እንደሚችል በተለያዩ አጋጣሚዎች ተመልክተናል፡፡
ቅናት በዚህ ልክ የሚገለጽ ከሆነ ይህን ስሜት ለመቆጣጠር ማድረግ ያለብን እና የሌለብን ነገሮች ምንድ ናቸው?
- በፍጥነት ድምዳሜ ላይ ከመድረስ መቆጠብ
የቅናት ስሜትን የሚያነሳሳ ሁኔታ በሚያጋጥም ጊዜ እርምጃ ከመውሰድ በፊት ሰከን ብሎ ሁኔታዎችን ማጤን ይገባል፡፡
የስው ልጅ እድገት ተመራማሪው ሲብል ሃርትስ ሰዎች የቅናት ስሜት ሲሰማቸው እንደ ሌሊት ወፍ በድንገት ከመስፈንጠራቸው በፊት ስሜቱን ምን ፈጠረው ፣ የጠረጠሩት ውይም የቀኑበት ምክንያት ምን ያህል እውነት ሊሆን ይችላል እንዲሁም ስሜቱን ተከትሎ የሚያሳልፉት ውሳኔ ምን ያህል ተገቢ እንደሚሆን ረጋ ብለው እንዲያጤኑ መክረዋል፡፡
- ስሜትን በቶሎ አለመንጸባረቅ እና መረጋጋት
የቅናት ስሜትን ተከትሎ ይህ ለምን ሆነ ፣ የመከዳት እና የመጎዳት ስሜት እና ሌሎችም አሉታዊ ስሜቶች ሊንጸባርቁ ስለሚችሉ፤ ሰዎች ከቁጥጥር ወጪ በመሆን በራሳቸው እና በሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረስን እንዲያስቡ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡
በዚህም ሰውነት እና ሰሜቶን መቆጣጠር መማር እጅን ማንቀሳቀስ በቀስታ ትንፋሽ መውሰድ እና ከየትኛውም ቀጣይ እርምጅ በፊት አንድ ሁለት ጊዜ ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል፡፡
- እራስዎ ላይ ጫና ከመፍጠር መታቀብ
ሰዎች በተለየየ መንገድ የቅናት ስሜት ሊፈጠርባቸው ቢችልም ከእነርሱ ማነስ ወይም መጉደል ጋር አያይዘው መመልከት እንደሌለባቸው የስነ ልቦና ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ ሰዎች ሊያደርጉት የሚችሉት ትክክለኛው መፍትሄ ሰሜቱን መቆጣጠር እንጂ ይህ ስሜት ለምን ተሰማኝ በሚል እራሳቸውን ማስተናነስ ወይም ዝቅ ማድረግ ለሌላ የተወሳሰበ የስነ ልቦና ችግር ሊያጋልጥ ይችላል፡፡
አራስን መጥላት ፣ ብቸኝነት እና የፍቅር ግንኙነት ለመመስረት ፍራቻን የመሳሰሉ ችግሮች ሁኔታውችን ከመጠን በላይ ከራስ ጋር ለማገናኘት በሚደረግ ጥረት የሚከሰቱ ችግሮች ናቸው፡፡
- ቅናትን የፍቅር ስሜት መገለጫ አድርጎ አለመውሰድ
አንዳንዶች በሚወዷቸው ላይ የሚቀኑት የፍቅራቸው መጠን ከፍተኛ በመሆኑ ወይም ፍቅራቸውን የሚያሳዩበት መንገድ አድርገው ይገልጹታል፤ ነገር ግን ይህ ትክክል አይደለም፡፡
ሰዎች የፍቅር አጋሮቻቸው ሲቀኑባቸው ጥቂትም ቢሆን የመፈለግ ወይም የመወደድ ስሜት ያጎናጽቸው ይሆናል፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ያለመታመን እና ሁልጊዜም በጥርጣሬ አይን እንደሚታዩ እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡
በሌላ በኩል የሚቀኑ ሰዎች ቅናታቸው ከራሳቸው ስሜት ሳይሆን በሚቀኑበት ሰው ካላቸው ፍቅር የመነጨ እንደሆነ አድርገው ይገልጹታል፤ የስው ልጅ እድገት ተመራማሪው ሲብል ሃርትስ ታድያ ይህ ችግሩን ማስታመም እንጂ መፍትሔ አይደለም ሲሉ ይናገራሉ፡፡
- የፍቅር አጋርን ለማስቀናት አለመሞከር
ብዙዎች ቅናትን የፍቅር ማረጋገጫ አድርገው በመውሰድ የፍቅር አጋራቸውን ለመፈተን ወይም የፍቅር ደረጃውን ለማወቅ የቅናት ስሜት ውስጥ ለመክተት የተለያዩ ሙከራዎችን ሲደርጉ ይስተዋላሉ፡፡
የፍቅር አጋራችሁ ስለእናንተ ያለውን የፍቅር መጠን ማወቅ ከፈለጋችሁ ይህን የምታውቁበት በርካታ መንገድ አለ የሚሉት የሰዎች እድገት ተመራማሪው፤ ለማስቀናት መሞከር ግን ሰዎችን ወደ ሌላ ቦታ ሊገፋ እንደሚችል እና የማይስተካከል ስህተትን ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡
ከዚህ ይልቅ ትክክለኛ ስሜትን የምትገላለጹበትን መንገድ መፍጠር፣ በግልጽ ማውራት አለፍ ካለም የፍቅር ወይም የትዳር አማካሪዎችን መጎብኘት የተሻለ አማራጭ ነው ተብሏል፡፡