የትራምፕ የልደት ቀን ብሄራዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር ረቂቅ ህግ ቀረበ
የአሜሪካ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዋሽንግተን የልደት ቀን ብሄራዊ በዓል ሆኖ ሲከበር ቆይቷል

ሪፐብሊካን ህግ አውጪዎች ዋሽንግተን ዱልስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በትራምፕ ስም እንዲሰየም መጠየቃቸው ይታወሳል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የልደት ቀን ብሄራዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር ረቂቅ ህግ ቀረበ።
ሪፐብሊካን የኮንግረንስ አባሏ ክላውዲያ ቴኒ የትራምፕ ልደት ቀን (ሰኔ 14) ብሄራዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር የሚጠይቅ ረቂቅ ህግ ማቅረባቸውን ዘ ሂል ዘግቧል።
የትራምፕ የልደት ቀን ከአሜሪካ የሰንደቅ አላማ ቀን ጋር በተመሳሳይ ቀን የፌደራል የህዝብ በዓል ሆኖ መከበር እንዳለበት ነው ረቂቁ የሚጠይቀው።
በኮንግረንሱ ኒውዮርክን የወከሉት ክላውዲያ ቴኒ "የጆርጅ ዋሽንግተን የልደት ቀን የፌደራል በዓል እንደሆነው ሁሉ ትራምፕም የአሜሪካ ወርቃማ ዘመን ፕሬዝዳንት ስለሆኑ የልደት ቀናቸው ብሄራዊ በዓል መሆን አለበት" ነው ያሉት በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ።
የትራምፕን የልደት ቀን የፌደራል በዓል እንዲሆን የቀረበው ረቂቅ ህግ መጽደቅ ፕሬዝዳንት ትራምፕ "ለአሜሪካ ከፍታ ያበረከቱት አስተዋጽኦ እየተወሳ እንዲቀጥል ያደርጋል"ም ብለዋል።
የአሜሪካ መስራችና የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዋሽንግተን የተወለዱት በፈረንጆቹ 1732 የካቲት 22 ነበር። ጆርጅ ዋሽንግተን ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ለማውሳት በየአመቱ የካቲት በገባ በሶስተኛው ሰኞ የፕሬዝዳንቶች ቀን ይከበራል።
"በአሜሪካ የዘመናዊ ታሪክ እንደ ዶናልድ ትራምፕ ያለ ፕሬዝዳንት አለገኘንም" የሚሉት የሪፐብሊካን የኮንግረንስ አባል ክላውዲያ ቴኒ ትራምፕ እንደ ጆርጅ ዋሽንግተን ሁሉ እየተወሱ እንዲዘልቁ የልደት ቀናቸው የህዝብ በዓል መሆን አለበት የሚል አቋማቸውን ገልጸዋል።
ሪፐብሊካኖች ፕሬዝዳንታቸውን ለማስደሰት የተለያዩ ረቂቆችን እያቀረቡ ሲሆን የዋሽንግተን ዱልስ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ስምን በትራምፕ ለመተካት ባለፈው ወር ረቂቅ ማቅረባቸው ይታወሳል።
የፕሬዝዳንት የስልጣን ዘመን ከሁለት ወደ ሶስት ከፍ እንዲል የሚጠይቅ ረቂቅም ባለፈው ወር መቅረቡ አይዘነጋም።
ዴሞክራቶች ግን ከሪፐብሊካኖች እየቀረቡ ያሉ ረቂቆችን እንደማይቀበሏቸው እየገለጹ ነው።
ቴኔስን የወከሉት ዴሞክራቱ ስቲቭ ኮሀን አሜሪካ እንደ ሀገር እንድትቀጥል ከተፈለገ "እንደ ትራምፕ አይነት ትርምስ የሚፈጥር ፕሬዝዳንት" ከሁለት ጊዜ በላይ መመረጥ የለበትም ማለታቸውን ዩኤስኤ ቱዴይ አስነብቧል።