በሜዲትራኒያን ባህር ላይ በደረሰ የሄሊኮፕተር አደጋ አምስት የአሜሪካ ወታደሮች ሞቱ
የአሜሪካ ወታደራዊ ሄሊኮፕተር መደበኛ ልምምድ ላይ እያለ ባጋጠመው ችግር ነው ተከሰከሰው
በእስራኤልና በሃማስ መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ አሜሪካ በአካባቢው የምታደርገው እንቅስቃሴ ጨምሯል
በሜድትራኒያን ባህር ምስራቀዊ ክፍል ላይ በደረሰ የሄሊኮፕተር አደጋ አምስት የአሜሪካ ወታደሮች መሞታው ተገለጸ።
ወታደራዊ ሄሊኮፕተሩ የመደበኛ ልምምድ አካል በሆነ መልኩ ነዳጅ በሚሞላበት ወቅት ችግር አጋጥሞት እንደተከሰከሰ የአሜሪካ ጦር አስታውቋል።
በእስራኤልና በሃማስ መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ አሜሪካ በሜድትራኒያን ባህር ምስራቀዊ ክፍል አካባቢ የምታደርገው እንቅስቃሴ ጨምሯል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለተጎጂዎች ሀዘናቸውን የገለጹ ሲሆን፤ የሀገሪቱ ሰራዊት አባላት “በየቀኑ ህይወታቸውን ለአገራችን መሰዋት እያደረጉ ነው” ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን አክለውም "ለሞቱት ወታደሮች ቤተሰቦች ሁሉ ዛሬ እና በየቀኑ እንጸልያለን" ሲሉም ተናግረዋል።
የአሜሪካ ጦር በአደጋው ዙሪያ ባወጣው ወታደራዊ መግለጫው፤ አውሮፕላኑ ከየት እንደተነሳ እና አደጋው የት እንደደረሰ አልገለጸም።
አሜሪካ ባሳለፍነው ወር ሁለት የአውሮፕላን ተሸካሚዎችን፣ እንዲሁም መርከቦችን እና ጄቶችን ወደ ምሥራቃዊ ሜዲትራኒያን አንቀሳቅሳለች።
አሜሪካ የጦር መርከቦቿን ወደ አካባቢው ያሰማራችው በእስራኤል እና በሃማስ መካከል ያለው ግጭት በሌሎች የቀጠናው አካባቢዎች ሊስፋፋ ይችላል በሚል ስጋት ነው ተቧል።
በተለይም በሊባኖስ የሚንቀሳቀሰው ሄዝቦላህ ቡድን የእስራኤል ሃማስ ጦርነትን እንዳይቀላቀል ለመከላከል አሜሪካ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላትም ተነግሯል።