
በግለሰቦቹ መካከል የነበረው የፖለቲካ ክርክር ወደ ድብድብ እንዲገቡ አድርጓቸዋል ተብሏል
120 ሺህ ዶላር ቅጣት የሚጠብቃቸው የአውሮፕላን ተሳፋሪዎች
የቱርኩ ፔጋሰስ የተሰኘው አውሮፕላን ከአንታሊያ ወደ ካዛኪስታኗ አስታና ከተማ መንገደኞችን ጭኖ ሲጓዝ ነበር፡፡
አየር መንገዱ በረራውን በጀመረ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ በተሳፋሪዎች መካከል አለመግባባት ይከሰታል፡፡ ጸቡ የተነሳው ሁለት የካዛኪስታን ሴት መንገደኞች የዩክሬን ዜግነት ካላቸው ባልና ሚስቶች ጋር ነበር፡፡
እነዚህን መንገደኞች ወደ ጸብ የወሰዳቸው ደግሞ በመካከላቸው የነበረ የፖለቲካ ሀሳብ ክርክር እንደሆነ የቱርክ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ በመንገደኞቹ መካከል የነበረው የፖለቲካ ክርክር ወደ አለመግባባት እና ጸብ አምርቶ ሊደባደቡ ችለዋል፡፡
በመንገደኞቹ መካከል የነበረው ድብድብ ከባድ እና መድማት ጭምር የነበረው መሆኑን ተከትሎ የአውሮፕላኑ አብራሪ በረራውን ለማቋረጥ እና ለማረፍ ተገዷል ተብሏል፡፡
ኢርዙሩም ኤርፖርት ለማረፍ የተገደደው ይህ አውሮፕላንም ተደባባዳቢዎቹን ለፖሊስ ካስረከበ በኋላ ዳግም በረራውን እንደቀጠለ ተገልጿል፡፡
ተደባዳቢዎቹ በመጀመሪያ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል የተባለ ሲሆን ከህክምና በኋላ በመጨረሻም ፖሊስ ወደ እስር ቤት ወስዷቸዋል፡፡
መንገደኞቹ በበረራው ላይ ባደረሱት ጉዳት ምክንያት የ120 ሺህ ዶላር ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ተገልጿል፡፡
እነዚህን መንገደኞች ለጸብ የዳረጋቸው ጉዳይ መነሻው የፖለቲካ አለመግባባት ነው ቢባልም በግልጽ ጉዳዩ በዘገባው ላይ አልተጠቀሰም፡፡