አሜሪካ ከዋሽንግተኑ ግጭት በኋላ የሄሊኮፕተር በረራን ከለከለች
ባሳለፍነው ረቡዕ በሬገን ብሔራዊ ኤርፖርት አቅራቢያ አውሮፕላን እና ሄሊኮፕተር ተጋጭተው 67 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል
አደጋውን ተከትሎ እስካሁን የ41 ሰዎች አስክሬን የተገኘ ሲሆን ቀሪ አስክሬኖች እየተፈለጉ ነው
አሜሪካ ከዋሽንግተኑ ግጭት በኋላ የሄሊኮፕተር በረራን ከለከለች፡፡
የአሜሪካ ባለስልጣናት ረቡዕ በሬገን ዋሽንግተን ብሔራዊ ኤርፖርት አቅራቢያ የተከሰተውን አደጋ ተከትሎ የሄሊኮፕተር በረራዎችን አግደዋል፡፡
መርማሪዎች የበረራ መረጃዎችን እና በበረራ ክፍል ውስጥ ያሉ ድምጾችን የያዘውን የሄሊኮፕተሩን ጥቁር ሳጥን (ብላክ ቦክስ) ማግኘት ችለዋል፡፡
የብሔራዊ ትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ አባል ቶድ ኢንማን በመንገደኞች አውሮፕላን እና ወታደራዊ ሄሊኮፕተር መካከል በተፈጠረው ግጭት 67 ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጠዋል።
በአሜሪካ ታሪክ ከሁለት አስርተ አመታት ወዲህ አስከፊ እንደሆነ የተነገረለትን አደጋ መንስኤ በትላንትናው ዕለት የተገኝው ጥቁር ሳጥን ውስጥ የሚኖረው መረጃ ፍንጭ ሊሰጥ እንደሚጥል የአደጋው መርማሪዎች ተናግረዋል፡፡
ግጭቱን ተከትሎ በፖቶማክ ወንዝ ውስጥ ከገባው የአውሮፕላን 41 አስክሬን የወጣ ሲሆን ተጨማሪ አስክሬኖችን የማፈላለግ ስራ አሁንም ቀጥሏል፡፡
የብሔራዊ ትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች እና በአደጋው ወቅት በሬገን ኤርፖርት ማማ ውስጥ ተረኛ የነበረውን ብቸኛ የአየር ተቆጣጣሪን ቃል ተቀብሏል፡፡
የደህንነት ቦርዱ አባል ቶድ ኢንማን የአደጋው መንስኤ ተጣርቶ ከመታወቁ በፊት ምንም አይነት መላምት ለማስቀመጥ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸው ዋነኛ ትኩረታችን ተመሳሳይ አደጋ በቀጣይ እንዳይከሰት መከላከል ነው ብለዋል፡፡
የአሜሪካ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሼን ዱፊ አደጋውን ተከትሎ በሬገን ኤርፖርት አቅራቢያ እና በዋሽንግተን የሄሊኮፕተር በረራዎች ላልተወሰነ ጊዜ ተገድበው እንዲቆዩ ውሳኔ መተላለፉን ይፋ አድርገዋል፡፡
በዚህም ከወታደራዊ ፣ ከህክምና ፣ የአየር ደህንነት መቆጣጠሪያ እና ፕሬዝዳንታዊ ሄሊኮፕተሮች ውጪ በአካባቢው የንግድ እና የመንገደኞችን ጨምሮ በአጠቃላይ የሄሊኮፕተር በረራዎች ታግደዋል ነው ያሉት ሚኒስትሩ፡፡
ክልከላው የረቡዕ አደጋ መንስኤ ምርመራ ተጣርቶ ይፋ እስከሚደረግበት ጊዜ ድረስ ቢያንስ ለ30 ቀናት የሚቆይ ይሆናል፡፡
የአሜሪካ ኤርላይንስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሮበርት ኢሶም አየር መንገዱ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር የአካባቢውን የአየር ጉዞ ደህንነት የተጠበቀ ለማድረግ ይተባበራል ብለዋል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ2017- 2019 ድረስ በነበሩ ሶስት አመታት ውስጥ ከሬገን ብሔራዊ አውሮፕላን ማረፊያ 48 ኪሜ ርቀት ላይ በቀን በአማካይ 80 የሄሊኮፕተር በረራዎች ይደረጋሉ፡፡