ናይል፣ ኮርዶፋን እና ዳርፉር አካባቢዎች ደግሞ በጎርፍ አደጋው የተጎዱ ግዛቶች ናቸው
በሱዳን በተከሰተ ጎርፍ በትንሹ 52 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
በሱዳን ባጋጠመ ከፍተኛ ዝናብ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ በትንሹ 52 ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በርካቶች ደግሞ አካላዊ ጉዳትን አስተናግደዋል፡፡
እንደ ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘገባ ከሆነ ሱዳን ከግንቦት እስከ ጥቅምት ድረስ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ በየዓመቱ በርካታ ሰዎች እና ንብረት በጎርፍ መጥለቅለቅ ምክንያት ትጎዳለች፡፡
በትናንትናው ዕለትም በበኮርዶፋን፣ ናይል እና ደቡባዊ ዳርፉር ግዛቶች በጣለ ከባድ ዝናብ ምክንያት በትንሹ 52 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
የሱዳን ብሄራዊ የዜጎች ደህንነት ተቋም ቃል አቀባይ የሆኑት አብደል ጃሊል አብደልርሂም እንዳሉት በሶስቱ ግዛቶች ከሞቱት ዜጎች በተጨማሪ ከስምንት ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶች በጎርፍ ወድመዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ጎርፉ ከግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች ባለፈ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት መሰረተ ልማቶች የግለሰቦች ኢንቨስትመንት ስራዎች መውደማቸውንም ቃል አቀባዩ አክለዋል፡፡
የተመድ ሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ባወጣው የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሪፖርቱ በዘንድሮው የክረምት ወራት ውስጥ 38 ሺህ አባወራዎች ከቀላል እስከ ከባድ የጎርፍ አደጋ ሰለባ ናቸው ብሏል፡፡
በሱዳን ከአንድ ዓመት በፊት 314 ሺህ ዜጎች በጎርፍ አደጋ ተጎድተው እንደነበር ይሄው ተቋም ያሳወቀ ሲሆን የያዝነውን ነሀሴ ወር ጨምሮ በቀጣዮቹ ሶስት ወራት ውስጥ ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ተገልጿል፡፡
ሱዳን የኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብ የውሃ እጥረት እንዲያጋጥም ያደርጋል የሚል ሀሳብ በተደጋጋሚ የምትናገር ሲሆን ኢትዮጵያ በበኩሏ ግድቡ ሱዳን በጎርፍ አደጋ እንዳትጥለቀለቅ ይጠቅማል በማለት ላይ ትገኛለች፡፡