የፓኪስታን አንድ ሶስተኛ መሬት በውሃ መሸፈኑ የሀገሪቱ አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ገለጸ
የፓኪስታን አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ሼሪ ሬህማን ዝናቡ “ሊታሰብ የማይቻል ቀውስ ፈጥረዋል” ብለዋል
እስካሁን በጎርፍ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 1ሺ 33 መድረሱን አሃዛዊ መረጃ ያሳያሉ
ከባድ በሆነው የክረምት ዝናብ ምክንያት የፓኪስታን አንድ ሶስተኛው መሬት በውሃ መሰፈኑን የሀገሪቱ አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የፓኪስታን አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ሼሪ ሬህማን ዝናቡ “ሊታሰብ የማይቻል ቀውስ ፈጥረዋል” ብለዋል።
ሚኒስትሯ ፤“ አንድ ትልቅ ውቅያኖስ ነው የሆነው፣ ውሃውን የሚወጣበት ደረቅ መሬት የለም” ሲሉ መናገራቸውም ነው ኤኤፍፒ የዘገበው፡፡
በፓኪስታን ከሰኔ ወር ጀምሮ የዘነበው ያልተጠበቀው ክረምት ዝናብ 33 ሚሊዮን በሚሆኑት የሀገሪቱ ህዝቦች ከባድ ጉዳት እንዳስከተለ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
እስካሁን በጎርፍ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 1ሺ33 መድረሱን የሀገሪቱ ብሔራዊ የአደጋ መከላከል ባለስልጣን ገልጿል።
በ24 ሰአታት ብቻ 119 ሰዎች የሞቱበት የትናንትናው እለት አሳዛኝ ክስተትም የሚታወስ ነው፡፡
በተለይም በሀገሪቱ ደቡብ ምስራቅ ክልል ውስጥ የምትገኝ የሲንዲ ግዛት ያጋጠመው የጎርፍ መጥለቅለቅ በፈረንጆቹ በ2010 ከነበረው የከፋ መሆኑን ተገልጿል።
በፈረንጆቹ በ2010 በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ቢያንስ 1 ሺህ 700 ፓኪስታናውያን የገደለ ሲሆን አብዛኛዎቹ የሲንዲ ግዛት ነዋሪዎች እንደነበሩ አይዘነጋም።
እናም አሁን ላይ ከፍተኛ መጠን ባለው ጎርፍ አደጋ የተጎዳችው ፓኪስታን ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንደምትሻ እየተነገረ ነው፡።
አስካሁን ባለው መረጃ፤ ቻይና በጎርፉ ምክንያት ለተፈናቀሉ ፓኪስታናውያን የሚሆኑ 25 ሺህ ድንኳኖችን እና የእርዳታ ቁሳቁሶችን ጨምሮ የአስቸኳይ ጊዜ ሰብአዊ ዕርዳታ አንደላከች ታውቋል፡፡