በቀሪዎቹ የክረምት ጊዜ ቅጽበታዊ ጎርፍ እንደሚከሰት የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለፀ
ህብረተሰቡ ራሱን ከመብረቅ አደጋ እንዲጠብቅ የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰቧል
በአዋሽ፣ ተከዜ፣ ጣና፣ ባሮ አኮቦና የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉም አስጠንቅቋል
በኢትዮጵያ የክረምት ወራት የሚባሉት ከሰኔ እስከ መስከረም ያሉት አራት ወራት ሲሆኑ ሀምሌ እና ነሀሴ ደግሞ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ የሚገኝባቸው ወራት ናቸው።
አል ዐይን አማርኛ የያዝነውን ነሀሴ ወር ጨምሮ የቀጣዮቹ ሁለት የክረምት ወራት ምን ሊመስሉ ይችላሉ ሲል የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩትን ጠይቋል።
በኢንስቲትዩቱ የቅድመ ትንበያ ዳይሬክተር ጫሊ ደበሌ እንዳሉት አሁን ያለንበት ወቅት ከፍተኛ መጠን ዝናብ የምናገኝበት ወቅት መሆኑን ጠቅሰው በዛው ልክ አደጋዎች የሚበዙበት ነው ብለዋል።
“አፈሩ እርጥበት አግኝቶ ውሃ የጠገበበት በመሆኑ የሚዘንበው ዝናብ በቀላሉ ወደ ጎርፍነት ይቀየራል።
በተለይም በነሀሴ ወር ላይ ለአጭር ሰዓት ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ሊዘንብ እንደሚችል ትንበያው ያስረዳል። ቅጽበታዊ ጎርፍ የመከሰት እድሉም ከፍተኛ ነው” ሲሉም ዳይሬክተሯ አክለዋል።
በመሆኑም ህብረተሰቡ እና ተቋማት የፍሳሽ መስመሮችን መክፈት፣ በማሳዎች ላይ ውሃ እንዳይተኛ እና መንገደኞችም ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት አካባቢያቸውን በደንብ እንዲቃኙም አሳስበዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ወቅቱ ለመብረቅ አደጋ መፈጠር ምክንያት የሆኑት ለመሬት ቅርብ የሆኑ ሞቃታማ የዳመና ነጠብጣቦች እና እና ከፍታ ቦታዎች ላይ ያሉ ቀዝቃዛ የዳመና ነጠብጣቦች የመገናኘት እድሉ ሰፊ የሚሆንበት ወቅት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ህብረተሰቡ ራሱን ከመብረቅ አደጋዎች ለመከላከል በተለይም ዝናብ በሚዘንብባቸው ወቅቶች ራሱን ኤሌክትሪክ ከሚያስተላልፉ ቁሳቁሶች እንዲያርቅ አሳስበዋል፡፡
ለአብነትም በዝናብ ወቅት ዛፍ ስር እና ከፍታ ቦታዎች ላይ ከመቀመጥ፣ በዝናብ ወቅት ስልክ ከማውራት፣ ተሸከርካሪ ከመንዳት እና ብረት ከመንካት እንዲቆጠቡ ዳይሬክተሯ አሳስበዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለም በአዋሽ፣ ተከዜ፣ ጣና፣ ባሮ አኮቦ እና የስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ አካባቢዎች የጎርፍ እና ውሃ መጥለቅለቅ አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉም አስጠንቅቀዋል፡፡
ህዝቡ እና የድንገተኛ አደጋ ቁጥጥር እና ሌሎች የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሰዎች ላይ እና ንብረቶች ላይ አደጋዎች እንዳይደርሱ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
ዳይሬክተሯ አክለውም ሀምሌ ወር ለይ ይገኝ የነበረው የዝናብ መጠን በነሀሴ ወር ላይም ይቀጥላል ያሉ ሲሆን የዘንድሮው ክረምት በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ዘግይቶ እንደሚወጣም አክለዋል።
ሶማሊ ክልል ጉጂ፣ ቦረና እና ለነዚህ ቦታዎች አጎራባች የሆኑ የደቡባዊ ኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች በክረምት ወቅት ዝናብ እያገኙ አይደለም።
ከላይ የተጠቀሱት አካባቢዎች ዝናብ የሚያገኙት በበልግ እና በጋ ወቅቶች ላይ ብቻ መሆኑን ከኢንስቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።