በሱዳን በጎርፍ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 100 ደረሰ
አሁንም የከፋ የጎርፍ አደጋ ሊኖር የሃገሪቱ የአደጋ መከላከል ባለስልጣናት አስጠንቅቀዋል
የዓባይ ወንዝ የውሃ መጠን በመጪዎቹ ቀናት የበለጠ ሊጨምር እንደሚችልም ተገምቷል
በሱዳን ሰሞኑን በደረሰው የጎርፍ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር በ10 ጨምሮ 100 ደርሷል፡፡
የዓባይ ወንዝ የውሃ መጠን በመጪዎቹ ቀናት የበለጠ ሊጨምር እንደሚችልም የገለፁት የሃገሪቱ የአደጋ መከላከል ባለስልጣናት አስጠንቅቀዋል።
ባለስልጣናቱ በዚህ ወር ብቻ ባጋጠመ አደጋ 99 ሱዳናውያን መሞታቸውንና 93 ደግሞ መጎዳታቸውን አስታውቀዋል።በድምሩ 23 ሺ 724 ቤቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውንና 35 ሺ 225 ያህል ቤቶች ደግሞ መጎዳታቸውንም ተናግረዋል ባለስልጣናቱ።
መሠል የጎርፍ አደጋዎች ለሱዳን አዲስ አይደሉም። ክረምት በመጣ ቁጥርም ያጋጥማል። ሆኖም ዘንድሮ በ1940ዎቹ ካጋጠመውና የከፋ ነበር ከተባለለት የበለጠ የጎርፍ አደጋ ማጋጠሙ ነው የተነገረው።
አደጋው ካለፉት ሁለት የክረምት ወራት ይልቅ በነሐሴ እና መስከረም ወራት ይከፋል መባሉም ብዙዎችን አስግቷል።
"መጪው ወሳኝ ሳምንት ነው፤ በከፍተኛ ሁኔታ መዘጋጀትንም ይጠይቃል" ሲሉ ነው የአደጋውን ሁኔታ የሚከታተለውን ኮሚቴ የሚመሩ አንድ የሃገሪቱ መስኖ ሚኒስቴር ዳይሬክተር የተናገሩት።
አል ጀዚራ፣ አል መናቂል እና ሲናርን የመሣሠሉ የሃገሪቱ ግዛቶች በአደጋው ክፉኛ እንደተጎዱ ተጎድተዋል ተብሏል፡፡በደቡባዊ ካርቱም በሚገኘው አል ጀዚራ ግዛት ብቻ 31 መንደሮች በጎርፍ ተጠርገው ተወስደዋል።