ኢራን የስለላ ቡድኑ አባላት መረጃ ሲሰበሰቡ እና ጸረ -ኢራን የሆነ ፕሮፖጋንዳ ሲጽፉ ነበር ብላለች
የኢራን የደህንነት ድርጅት እንዳስታወቀው ኢራን ወሳኝ በሆኑ ዘርፎች ላይ መረጃ ለመሰብሰብ ሲንቀሳቀስ የነበረ የእስራኤል የስለላ ኔትዎርክ ይዛለች።
በቴህራን ያለው የአል ዓይን ኒውስ ጋዜጠኛ ያየው የኢራን የደህንነት ድርጅት መግለጫ፣ የእስራኤሉ ሞሳድ አካል የሆነው መረብ ተበጥሷል፤ኪሳራም ደርሶበታል ብሏል።
መግለጫው የስለላ ቡድኑ አባላት ከእስራኤል ጋር የመስራት ታሪክ ካለው የተገንጣይ ቡድን አመራር ከሆኑት መካከል በአንዱ አማካኝነት ከሞሳድ ኃላፊ ጋር መገናኘታቸውን ጠቅሷል።
ከዚህ በተጨማሪም የስለላ ቡድኑ አባት መረጃ ሲሰበስቡ፣ የጦር መሳሪያ ስልጠና ሲወስዱ እንዲሁም ጸረ ኢራን የሆነ የፕሮፖጋንዳ መፈክር ሲጽፉ ነበር ብሏል መግለጫው።
የኢራን የደህንነት ሚኒስቴር የታሰሩት እነማን እንደሆኑ፣የየት ሀገር ዜጎች እንደሆኑ እና የት እንደታሰሩ ግልጽ አላደረገም።
ደህንነቱ ባለፈው ሳምንት ወሳኝ የሆነ ተቋም ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የነበሩ የእስራኤል የስለላ መረብ መያዙን ባለፈዉ ቅዳሜ ገልጾ ነበር።
ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ "ይህ የስለላ ኔትወረክ በሰሜን ኢራን በሚገኘው የኩርዲስታን ግዛት በኩል ወደ ኢራን ገብቷል፤ ፍንዳታ ለማድረስ የሚያስችል ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቀው የነበሩት የኔትውኩ አባላት በክትትል ተይዘዋል።"
ነገርግን የኩርዱ ኮምላ የተባለው ፖርቲ አባላቱ ከእስራኤሉ ሞሳድ ጋር ግንኙነት አላቸው የሚለውን ክስ አስተባብለዋል።