በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ለሩሲያ፣ ለቻይናና ለኢራን ክፍተት አንሰጥም- ፕሬዝዳንት ባይደን
የገልፍ ሀገራት-አሜሪካ የልማትና ደህንነት ጉባዔ በሳዑዲ አረቢያ ተካሄደ
ከሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ምርቷን በቀን ወደ 13 ሚሊዮን በርሜል ለማሳደግ መወሰኗን አስታውቃለች
የገልፍ ሀገራት-አሜሪካ የልማትና ደህንነት ጉባዔ በዛሬው እለት በሳዑዲ አረቢያ ጄዳህ ተካሂዷል።
በጉባዔው ላይ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፣ የሳዑዲ ልዑል አልጋ ወራሽ መሃመድ ቢን ሰልማን እና የአረብ ኢሚሬትስ ፕሬዝዳንት መሃመድ ቢን ዛይድን ጨምሮ ሌሎችም የገልፍ ሀገራት መሪዎች ተሳትፈዋል።
ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት የሳዑዲ ልዑል አልጋ ወራሽ መሃመድ ቢን ሰልማን፤ “ይህ የመሪዎች ጉባኤ ሀገሮቻችንን ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።
“ዘላቂ ልማትን ለማምጣት የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶች ያገናዘበ ሚዛናዊ አካሄድ መከተልን ይጠይቃል” ያሉት መሃመድ ቢን ሰልማን፤ የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶች ለመቋቋም የካርበን ልቀተን መቀነስ ልቀትን መሰረት ያደረገ አሰራር መከተላቸውን አስታውቀዋል።
ከነዳጅ ጋር ተያይዞ ሊያጋጥም የሚችል እጥረትን ለመቅረፍም ሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ምርቷን በቀን ወደ 13 ሚሊዮን በርሜል ለማሳደግ መወሰኗንም አስታውቀዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳነት ጆ ባይደንም በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ውስጥ ለሩሲያ፣ ለቻይናና ለኢራን ክፍተት አንሰጥም ብለዋል።
ኪራን ጋር በተያያዘ የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር ለማስቆም ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ እንፈልጋለን ያሉ ሲሆን፤ ነገረ ግን ኢራን መካከለኛው ምስራቅ ላይ ስጋት እንድትፈጥር አንፈቅድም ብለዋል።
ከየመን ጋር በተያያዘም የተኩስ አቁም ከታወጀ 15ኛ ሳምንቱ ላይ መሆኑን አስታውሰው፤ ውጥረቶች የሚቀንሱበት መንገድ ላይ እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
ባይደን አክለውም ለመሰረተ ልማት እና ለንጹህ የኃይል ልማት በቢሊየን የሚቆጠሩ ዶላሮችን ኢንቨስት እናደርጋለን ብለዋል።
የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ በበኩላቸው፤ ቀጠናው እና ሀገሮቻችን አሁን ዓለማችንን እያጋጠመ ላለው ችግር መፍትሄ ማፈላግ ላይ በጋራ ልንሰራ ይገባል ብለዋል።
በአረብ ሀገራት እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ያለውን አጋርነት ለማሳደግ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚያስፈልግም አሰታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት አልሲሲ አክለውም፤ ከእስራኤል ጋር ጎረቤትየሆነች ነጻነቷ የተጠበቀ የፍሊስጤም ሀገር የ1967 ድንበር ባከበረ መልኩ ሊመሰረት እንደሚገባ እና ይህም ሰላም እና መረጋጋትን ለማምጣት እንደሚረዳ ገልጸዋል።