የሩሲያው ጋዝፕሮም ከኢራን ጋር የ40 ቢሊዮን ዶላር ንግድ ስምምነት ፈጸመ
በስምምነቱት መሰረት ጋዝፕሮም ኢራን በቀን 100 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ጋዝ ማምረት የሚያስችላትን መሰረተ ልማት ይዘረጋል ተብሏል
የሩሲያ፣ ተርኪዬ እና ኢራን ፕሬዝዳንቶች በቴህራን እየተወያዩ ነው
የሩሲያው ጋዝፕሮም ከኢራን ጋር የ40 ቢሊዮን ዶላር ንግድ ስምምነት ተፈራረመ።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በኢራን ጉብኝት በማድረግ ላይ ናቸው።የፕሬዝዳንቱን ጉብኝት ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ስምምነቶችን ፈጽመዋል ተብሏል።
የሩሲያው ጋዝፕሮም የነዳጅ ኩባንያ ከኢራን አቻው ጋር የ40 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራርሟል ሲል አርቲ ዘግቧል።
ስምምነቱ ኢራን በሰሜናዊ የሀገሪቱ አካባቢ በቀን 100 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ተጨማሪ ነዳጅ እንድታመርት የሚያስችል መሰረተ ልማት ጋዝፕሮም ኩባንያ ይፈጽማል ተብሏል።
ቴህራን የሩሲያ፣ ተርኪዬ እና ኢራን የሶስትዮሽ ውይይት መድረክን በማስተናገድ ላይ ስትሆን የሶስቱም ሀገራት መሪዎች በመድረኩ ላይ ተገኝተዋል።
የሶስቱ ሀገራት መሪዎች ላለፉት በርካታ ዓመታት በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ላለችው ሶሪያ የተሻለ መፍትሄ መፈለግ በሚቻልበት ዙሪያ ይወያያሉ ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም የሶስቱ ሀገራት መሪዎች በተናጠል ዲፕሎማሲያዊ እና በአካባቢያዊ አጀንዳዎች ዙሪያ እንደሚወያዩ ተገልጿል።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ሩሲያ ጦሯን ወደ ዩክሬን የላከች ሲሆን ጦርነቱ ከተጀመረ አምስት ወራት ሊሞላው ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርቶታል።
በዚህ ጦርነት ምክንያትም ከአሜሪካ እና ምዕራባውያን ሀገራት ከስድስት ሺህ በላይ ማዕቀቦች የተጣሉባት ሩሲያ የእስያ እና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር አዳዲስ የንግድ ስምምነቶችን በማድረግ ላይ ትገኛለች።
ኢራን፣ ህንድ፣ ቻይና እና በተለያዩ አህጉራት የሚገኙ ሌሎች ሀገራት ደግሞ ከሩሲያ ጋር አዲስ የንግድ ስምምነቶችን በመፈጸም ላይ ናቸው።