ኢሰመኮ ጥቃት በደረሰባቸው የአፋር ክልል አካባቢዎች የክትትል ቡድኑን ማሰማራቱን አስታወቀ
ሕጻናት እና ተጋላጭ የማኅበረሰቦች ክፍሎች በማንኛውም ጊዜ ልዩ ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባም ነው ያሳሰበው
ኮሚሽኑ ግጭት ባገረሸባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች አደጋ ውስጥ የወደቁ ሲቪል ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣት እንዳሳሰበውም ገልጿል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሐምሌ 28 ቀን 2013 ዓ.ም ጥቃት በደረሰባቸው የአፋር ክልል አካባቢዎች የክትትል ቡድኑን ማሰማራቱን አስታወቀ፡፡
ኢሰመኮ የክትትል ቡድኑ በክልሉ ጉሊና ወረዳ፣ ጋሊኮማ ቀበሌ በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች እና ትምህርት ቤቶች ላይ በደረሰ ጥቃት በርካታ ቁጥር ያላቸው ሕጻናትን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መገደላቸው ሪፖርት ከተደረገ በኋላ መሰማራቱን አስታውቋል፡፡
ቡድኑ በአሁኑ ወቅት ለተጎጂዎች የሕክምና እርዳታ በሚደረግባቸው አካባቢዎች መሰማራቱንም ነው የገለጸው፡፡
ኮሚሽኑ ግጭት ባገረሸባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ስላለው ሁኔታም ክትትል እያደረግሁ ነው ያለም ሲሆን በግጭቱ ሳቢያ አደጋ ውስጥ የወደቁ ሲቪል ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎቱ በከፍተኛ ሁኔታ መባባሱ በእጅጉ እንደሚያሳስበው ገልጿል።
በግጭቱ ውስጥ የሚሳተፉ ሁሉም አካላት እና የፀጥታ ኃይሎች በሀገራዊም ሆነ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎችና በጦርነት ሕግና መርሆች የተጣለባቸውን ግዴታ እንዲያከብሩም ኮሚሽኑ በድጋሚ አሳስቧል፡፡
“ሲቪል ሰዎችና ታሪካዊ ቅርሶችን ጨምሮ ሲቪል መሰረተ ልማቶች ዒላማ መደረግ የለባቸውም፤ ሕጻናት እና ተጋላጭ ማኅበረሰቦች በማንኛውም ጊዜ ልዩ ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገባ የማኅበረሰብ ክፍሎች ናቸው”ም ነው ኢሰመኮ ያለው።