ህወሓት ኃይሎቹን በአስቸኳይ ከአማራ እና አፋር ክልሎች እንዲያስወጣ አሜሪካ አሳሰበች
ዋሽንግተን የአማራ ኃይሎች ከምዕራባዊ ትግራይ እንዲወጡም ጠይቃለች
የዩኤስ ኤይድ ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር ከሰሞኑ በምስራቅ አፍሪካ ጉብኝት በማድረግ ላይ ናቸው
የህወሓት ኃይሎች በአስቸኳይ ከአማራ እና አፋር ክልሎች እንዲወጡ አሜሪካ አሳሰበች።
ድጋፎችን ለሚፈልገው የትግራይ ህዝብ ማድረስ ካስፈለገ ሁሉም አካላት ግጭቶቹን ሊያቆሙ ይገባል ያሉት የአሜሪካ ህዝብ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስ ኤይድ) ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር ለግጭቱ ወታደራዊ መፍትሔዎች እንደሌሉ ገልፀዋል።
በመሆኑም አሜሪካ ህወሓት ኃይሎቹን በአስቸኳይ ከአማራ እና አፋር ክልሎች እንዲያስወጣ ጥሪ ታቀርባለች ነው ያሉት ሳማንታ ፓወር።
አንዳንድ የራያ አካባቢዎችን ተቆጣጥሯል የሚባልለት ህወሓት በአፋር በኩል ዘመቻዎችን መክፈቱ ይታወቃል።
የአማራ ክልል መንግስት ኃይሎቹን ከምዕራባዊ ትግራይ እንዲያስወጣም ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል መንግስት የተጠቀሱት አካባቢዎች ህወሓት ስልጣን ላይ በያዘበት ወቅት በግድ ወደ ትግራይ ክልል ያካተታቸው የአማራ ህዝብ አካባቢዎች ናቸው ሲል በተደጋጋሚ ይገልጻል።
ሳማንታ የኤርትራ መንግስትም ኃይሎቹን ከኢትዮጵያ በአስቸኳይ እና በዘላቂነት እንዲያስወጣም ጠይቀዋል።
ሆኖም የኤርትራ ጦር ከየትኞቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ነው በቶሎ የሚወጤው የሚለውን በውል አልጠቀሱም።
ሰብዓዊ ድጋፎች ያለ እንቅፋት ሊቀርቡ እና በትግራይ ያለው የመሠረተ ልማት እና የንግድ መቋረጥ የግድ ሊያበቃ እንደሚገባም አስታውቀዋል።
ሳማንታ ፓወር ከሰሞኑ በምስራቅ አፍሪካ የአምስት ቀናት ጉብኝት በማድረግ ላይ መሆናቸው ይታወቃል።
ከሰሞኑ በሱዳን በነበራቸው ጉብኝት ከተለያዩ የሃገሪቱ ባለስልጣናት ጋር መምከራቸውና ኡም ራኩባ የተሰኘውን በትግራይ ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች መጠለያ ጣቢያን መጎብኘታቸው የሚታወስም ነው።