ዩኒሴፍ፤ በአፋር ክልል የተገደሉ ዜጎች ጉዳይ አስደንጋጭ መሆኑን ገለጸ
በአፋር ክልል በመጠለያ ጣቢያ ላይ በተፈፀመ ጥቃት 107 ህጻናትን ጨምሮ የ240 ተፋናቃዮች ህይወት ማለፉ ይታወቃል
ዩኒሴፍ፤ ድርጊቱን የፈጸመውን አካል በመግለጫው ባያካትትም፤ የአፋር ክልል በበኩሉ ህወሓት ነው የፈፀመው ማለቱ ይታወሳል
በአፋር ክልል በተፈጸመ ጥቃት 107 ህጻናትን ጨምሮ የ240 ተፋናቃዮች መገደል አስደንጋጭ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት የህጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) አስታወቀ።
የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ሄንሪታ ፎር በአፋር ክልል በደረሰው ጥቃት ዙሪያ መግለጫ አውጥተዋል።
በአፋር ክልል በጤና እና ትምህርት ተቋማት ውስጥ የተጠለሉ 107 ህጻናትን ጨምሮ 240 ዜጎች መገደላቸውን መስማቱን የገለጸው ዩኔስኮ ይህም አስደንጋጭ እንደሆነ ጠቅሷል።
ከዚህ ባለፈም ዋነኛ የምግብ ማከማቻ መውደሙ እንዳሳሰበውም ነው ተቋሙ የገለጸው።
በአፋር ክልል እና በሌሎች የትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች እየተደረገ ያለው ውጊያ መባባሱ ለህጻናት አስከፊ መሆኑንም የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ሄንሪታ ፎር ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ዩኒሴፍ፤ በአፋር ክልል በተፈጸመ ጥቃት 107 ህጻናትን ጨምሮ የ240 ተፋናቃዮች መገደላቸውን ይግለጽ እንጅ፤ድርጊቱን የፈጸመው አካል የትኛው ወገን እንደሆነ ግን በመግለጫው ላይ አላካተተም።
የአፋር ክልል የኮሙኒኬሽን ቢሮ አርብ ዕለት ባወጣው መግለጫ የህወሀት ኃይሎችን ባደረሱት ጥቃት 107 ህጻናትን ጨምሮ 240 ተፋናቃዮችን መገደሉን መግለጹ ይታወሳል።
የአፋር ክልል ሰላምና አስተዳደር ቢሮ፤ ህወሃት በክልሉ ፈንቲረሱ ዞን ያሎ ወረዳ በንጹሃን አርብቶ አደሮች ላይ በከፈተዉ ድንገተኛ ጥቃት በሰዉና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን ሃምሌ ወር ላይ መግለጹ የሚታወስ ነው።
በሰሜን ኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው ጦርነት በርካታ ህጻናት ችግር ላይ እንዲወድቁ ማድረጉንም ተቋሙ አስታውቋል። ሁሉም ወገኖች አስቸኳይ የሰብዓዊ ተኩስ አቁም ትግበራን እንጀምሩም ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካች ምክር ቤት አሸባሪ በሚል የፈረጀው ህወሃት በአፋር ክልል በፈጸመው ጥቃት 107 ህጻናትን ጨምሮ የ240 ተፋናቃዮች መግደሉን የክልሉ መንግስት መግለጹ ይታወሳል።
የክልሉ መንግስት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መረጃ ህወሃት ከያሎና ጎሊና ወረዳዎች ተፈናቅለው ጋሊኮማ ጤና ጣቢያ እና ትምህርት ቤት ተጠልለው በነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ አርብቶ አደሮች ላይ “አሰቃቂ ጭፍጨፋ” አክሂዷል ብሏል።
በጥቃቱም በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ የነበሩ 107 ህጻናት፣ 89 ሴቶች እና 44 አዛውንቶች በድምሩ የ240 ሰዎች መሞታቸውን የመጀመሪያ ሪፖርት እንደደረሰው የክልሉ መንግስት የኮሙዩኒኬሽን አስታውቋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መንግስት ሀገረመንግስቱን አደጋ ላይ በሚጥል ተግባር ላይ ተሳትፏል ያለውን ህወሓትን በሽብርተኝነት መፈረጁ ይታወሳል።
በትግራይ ክልል በፌደራል መንግስትና ትግራይን ክልል ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል ግጭት ከተጀመረ ከ8 ወር በኋላ የፌደራል መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ፣መከላከያ ሰራዊቱን ከትግራይ ማስወጣቱ ይታወሳል።
የፌደራል መንግስት ሰራዊቱን ከትግራይ ያስወጣው የትግራይን ቀውስ በውይይት ለመፍታት በማቀዱ መሆኑን ቢገልጽም ግጭቱ አሁን ላይ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተስፏፍቷል።
ጥቅምት 24፣2013 በትግራይ ክልል የተጀመረው ግጭት አሁን ላይ ወደ አማራና አፋር ክልሎችም የተስፋፋ ተስፋፍቷል፡፡ መከላከያ ሰራዊትና የሁለቱ ክልሎች የጸጥታ አካላት የህወሓትን እንቅስቃሴ ለመግታት ጥቃት መክፈታቸውም መንግስት አስታውቋል።