በቡግና ወረዳ የተከሰተው የምግብ እጥረት አስቸኳይ ተጨማሪ እርዳታ ካልተደረገ የከፋ ጉዳት እንደሚያስከትል ተገለጸ
በዞኑ ቡግና ወረዳ 65 በመቶ ህጻናት እና 84 በመቶ እናቶች ለምግብ እጥረት መጋለጣቸው ጥናት አመልክቷል

በአካባቢው ድጋፍ እያደረጉ የሚገኙ የእርዳታ ድርጅቶች በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች የሚደርስባቸው መስተጓጎል የድጋፍ ስርጭቱ ላይ እክል መፍጠሩን ተናግረዋል
በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ ህጻናት እና እናቶችን ጨምሮ 10 ሺ የሚጠጉ ሰዎች ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን ወረዳው አስታውቋል፡፡
ከሰሞኑ በከፍተኛ የምግብ እጥረት ምክንያት የተጎሳቆሉ እናቶች ቆዳቸው የተሸበሸበ እና የገረጡ ህጻናትን አቅፈው የሚያሳዩና ለማየት የሚረብሹ ምስሎች የያዙ ዘገባዎች በሰፊው ወጥተዋል።
በክልሉ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግስት መካከል በተፈጠረው ግጭት ለአለፈው አንድ አመት በፋኖ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር በሚገኘው የቡግና ወረዳ ከግጭቱ በተጨማሪ አካባቢው ያጋጠመው የተፈጠሮ አደጋ ለችግሩ መንስኤ መሆኑን የወረዳው አስተዳደር ለአል ዐይን አማርኛ ገልጿል።
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጌታየ ካሳው አካባቢው ዝናብ አጠር ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ድርቅ የሚከሰትበት ቦታ መሆኑን ጠቅሰው በ2016/17 የምርት ወቅት ያጋጠመው ጎርፍ እና የምርት በበረዶ መመታት ሁኔታውን እንዳባባሰው ይገልጻሉ።
አካባቢው ተፈጥሯዊ አደጋዎች የሚፈራረቁበት ቢሆንም እስከዛሬ በነበረው አሰራር የግብርና ባለሙያዎችን በማሰማራት የግብርና ስርአቱን እና የምርት አሰባሰብ ሂደቱን ከጉዳት ለመጠበቅ ጥረት ይደረግ ነበር፡፡
አስተዳዳሪው እንደሚሉት ከ2015/16 የምርት ዘመን ጀምሮ አርሶ አደሩ ምንም አይነት ማዳበርያ እና የግብርና ግብአት አልደረሰውም፤ ከዚህ ባለፈም አልፎ አልፎ የምግብ እጥረት የሚያጋጥማቸው ነዋሪዎች ሲኖሩም ከተለያዩ አካላት ጋር በመነጋጋር ድጋፍ በማድረግ የጉዳት መጠኑን ለመቀነስ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ባለፈው አንድ አመት ግን በግጭቱ ምክንያት ይህን ማድረግ አልተቻለም ብለዋል አቶ ጌታየ።
በአሁኑ ወቅት ወረዳው ሙሉ ለሙሉ በፋኖ ታጣቂዎች ስር መሆኑን ተከትሎ አስተዳደሩን ወደ ላሊበላ ከተማ በማዘዋወር ችግሩን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ የተናገሩት አቶ ጌታየ፤ የችግሩ ሁኔታ ከሴቶች እና ህጻናት ተሻግሮ በአረጋውያን እና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችም ላይ መስተዋል መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
አቶ ጌታየ እንደገለጹት በወረዳው ሙሉ ለሙሉ የምግብ እጥረት የተከሰተ ሲሆን በተለይም ዘብሎ፣ ቋሮ ፣ ፈልፈሊቅ ፣ ብርኮ ፣ ጉልሀ እና ሌሎችንም ጨምሮ ከሰባት በላይ ቀበሌዎች ችግሩ የከፋባቸው ናቸው ብለዋል።
ወረዳው በጤና ጽ/ቤቱ ያስጠናው ጥናት እንደሚያመለክተው አሁን ላይ 7ሺህ ከአምስት አመት በታች ህጻናት እና 3 ሺህ እናቶች ለምግብ እጥረት ተጋልጠዋል፡፡
በጸጥታ ችግሩ ምክንያት መድሀኒቶችን ፣ አልሚ ምግቦች እና ሌሎች መሰረታዊ ቁሳቁሶችን ማድረስ ባለመቻሉ 65 በመቶ የወረዳው ህፃናት እና 84 በመቶ እናቶች በአጣዳፊ የምግብ እጥረት ውስጥ መሆናቸውን ይህ ጥናት አመልክቷል።
የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ጌታየ ይህ የቁጥር መረጃ የተገኘው ለክትባት በተሰማሩ የጤና ባለሙያዎች መሆኑን ገልጸው ሙሉ ለሙሉ የጉዳት መጠን ደረጃ ጥናት ቢሰራ ቁጥሩ ከዚህም ሊጨምር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በወረዳው የሚሰሩ ሁለት ባንኮች በጸጥታው ችግር ምክንያት ስራ አቁመዋል፤ በዚህ የተነሳም ሰዎች በባንክ ያላቸውን ገንዘብ አውጥተው ቀለብ ለመሸመት አልያም መሰረታዊ የምግብ ግብአቶችን ለማሟላት አይችሉም፤ "በ2016 /17 አመት አርሶ አደሩ የዘራውም በእጁ ላይ የሚገኘውን ጥቂት ዘር ነው እርሱንም በረዶ መቶበታል በዚህ ምክንያት ሁኔታዎች በአስከፊ ደረጃ ላይ ይገኛሉ" ብለዋል፡፡
ካለፈው አመት ሀምሌ ወር ጀምሮ የቡግና ወረዳን ጨምሮ በሰሜን ወሎ ሌሎች አካባቢዎች እየሰሩ የሚገኙ ሁለት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የእርዳታ ድርጅት ሰራተኞች በፋኖ ቁጥጥር ስር ወደሚገኙ ስፍራዎች ድጋፎችን ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ በመንግስት የጸጥታ አካላት ክልከላ ሲደረግባቸው መቆየቱን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
አንድ በአረጋውያን ሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚሰራ ገብረ ሰናይ ድርጅት ባለሙያ እንደሚለው ድጋፎች በፋኖ እጅ ሊወድቁ ይችላል በሚል መድሀኒትን ጨምሮ የአልሚ ምግቦችን ወደ ወረዳ እና ቀበሌዎች እንዳናደርስ የጸጥታ አካላት ክልከላ ያደርጉብናል፤ አንዳንዴም በሀላፊዎች ጫና እና ረጅም ጊዜ በወሰደ ግንኙነት በተገኘ ፈቃድ ድጋፍ ለማድረግ ወደ አካባቢዎቹ ስንንቀሳቀስ በየኬላዎቹ የሚገጥመን ፍተሻን ጨምሮ ሌሎች ተግዳሮቶች ተጎጂዎች ጋር በቶሎ እንዳንደርስ መሰናክል ሆኖብን ቆይቷል።
በቡግና ወረዳ ያጋጠመው የምግብ ዕጥረት ይፋ ከተደረገ በኋላ ግን በእንቅስቃሴ ገደቦች ዙርያ መሻሻሎች እንዳሉ ባለሙያው ይናገራል፡፡
ከዚህ ባለፈም በወረዳው በሚገኘው ከፍተኛ የመጠጥ ውሀ እጥረት የተነሳ አካባቢው ዝናብ አጠር ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ማህበረሰቡ የወንዝ እና ንጽህናቸው ያልተጠበቁ ውሀዎችን ለመጠጥነት እየተጠቀመ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡
ይህም ከምግብ እጥረቱ ባሻገር ተጨማሪ ውሀ ወለድ በሽታዎችን እና ወረርሽኞችን ሊያስከትል እንደሚችል አል ዐይን አማረኛ ያገኝው መረጃ ያመላክታል፡፡
የአማራ ክልል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ፎረም በክልሉ የተከሰቱ ጦርነት እና ግጭቶች በጤናው ዘርፍ ላይ ያደረሱትን ጉዳት አስመልክቶ በቅርቡ ይፋ ባደረገው ጥናት፤ የመንገድ መዘጋት እና የእንቅስቃሴ ገደብ አስፈላጊ መድኃኒቶችን፣ የሕክምና መሣሪያዎችን እና አቅርቦቶችን ለማጓጓዝ በከፍተኛ ደረጃ እንቅፋት ስለመሆኑ ማመላከቱ ይታወሳል፡፡
የህክምና ግብአቶች እና የምግብ ድጋፍ ስርጭት መስተጓጎሎ የትኛውም አካል ቢፈጽመው ከዓለም አቀፍ ህግ ጋር የሚቃረን እና የሰብአዊነት መርሆዎችን የሚጥስ ነው ብሏል ፎረሙ።
በላሊበላ እና አካባቢው በሚገኙ ቀበሌ እና ወረዳዎች ላይ የሚሰራ ሌላ የእርዳታ ድርጅት ባለሙያ በበኩሉ "በስፍራው የሚገኙ የረድኤት ድርጅቶች ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት መከላከል የሚችሉበት የምግብ እና የመድሀኒት ክምችት ቢኖራቸውም በጸጥታው ችግር ምክንያት በበቂ ተንቀሳቅሰው መስራት አልቻሉም፤ እኛ በምንሰራባቸው የላሊበላ ዙርያ ከቡግና ወረዳ በተጨማሪ ለምግብ ዕጥረት ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን እየተመለከትን እንገኛለን" ብሏል፡፡
በሰሜን ወሎ ዞን አንድ አንድ አካባቢዎች ያጋጠመው የምግብ እጥረት በስፍራው ከሚገኙ የእርዳታ ድርጅቶች በተጨማሪ ሌሎች የአለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ እና ትኩረትን እንደሚጠይቅ ባለሙያው ገልጿል፡፡
የቡግና ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጌታየ ካሳው በጸጥታ ሀይሎች ሲደረግ የነበረው ክልከላ ከደህንነት ስጋት እና እርዳታዎቹ ለታለመላቸው አለማ መዋላቸውን ማረጋጋጥ ስለሚገባ ነው ይላሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት ከዞን እና ከሌሎች የጸጥታ አመራሮች ጋር በመነጋገገር እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎችን በማስተባበር አመልድን ጨምሮ ወደ አራት የሚጠጉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች መድሀኒት ፣ የአልሚ ምግብ የገንዘብ ድጋፍ እና ሌሎች እርዳታዎችን እያደረጉ እንደሚገኙ አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡
በወረዳው ባጋጠመው የምግብ እጥረት ለ3 ወራት የሚያቆይ የመድሀኒት እና ሌሎች መሰረታዊ ድጋፎች ቢገኝም አፋጣኝ ተጨማሪ ድጋፎች ካልተደረጉ ጉዳቱ ሊከፋ እንደሚችል ተሰምቷል፡፡
የአሜሪካ ኢምባሲ በቡግና ወረዳ የተከሰተውን የምግብ እጥረት ቀውስ በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን ትናንት ምሽት በፌስቡክ ገጹ ባወጣው አጭር መግለጫ አስታውቋል።
በአሁኑ ወቅት አጋሮቻችን በጣም ለተጎዱ አካባቢዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ እየጨመሩ ነው ያለው ኢምባሲው ሁኔታውን እንደሚከታተለው እና ችግሩ መፍትሄ እንዲያገኝ እንደሚሰራ ገልጿል።
አል ዐይን አማረኛ በወረዳው ስላጋጠመው የምግብ እጥረት ያጋጠመውን የምግብ እጥረት በተመለከተ መረጃ ለማግኘት ወደ አማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ለቀናት ተደጋጋሚ የስልክ ሙከራዎችን ቢያደርግም ምላሽ ማግኝት አልቻለም፡፡
ነገርግን የክልሉ የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ በጸጥታ ችግር ምክንያት የተስተጓጎለው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እየተጓጓዘ መሆኑን ለብሔራዊው ቴሌቪዥን ኢቢሲ ትናንት ምሽት ተናግረዋል።