በጦርነቱ ምክንያት 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ህጻናት ከትምህርት ውጪ እንደሆኑ ተገልጿል
የሰብዓዊ ቀውስ በአማራ ክልል
የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ አደራጃለሁ የሚል ውሳኔ ካስተላለፈበት ሚያዝያ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ መካከል ጦረነት በመካሄድ ላይ ነው፡፡
የአማራ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉባኤ ከሰሞኑ በክልሉ ባለው የሰብዓዊ ቀውስ ዙሪያ ያለመ መድረክ በአዲስ አበባ አካሂዷል፡፡
የክልል እና የፌደራል ተቋማትን ጨምሮ በርካታ ሀገር በቀል እና ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች በተካፈሉበት በዚህ መድረክ ላይ በአማራ ክልል ያሉ የሰብዓዊ ቀውስ ሪፖርቶች ቀርበዋል፡፡
ከነዚህም መካከል አሁን ላይ 6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ያፈልጋቸዋል የተባለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ያህሉ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ የሚፈልጉ ናቸው ተብሏል፡፡
እንዲሁም 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ህጻናት በጦርነቱ ምክንያት ከትምህርት ውጪ ሆነዋል የተባለ ሲሆን አራት ሚሊዮን ገደማ ዜጎች ደግሞ የጤና አገልግሎት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡