በአማራ ክልል 15 ሺህ ንጹሀን ለሞት፣ ለአካል ጉዳትና አስገድዶ መድፈር መጋለጣቸው ተነገረ
በክልሉ ከ2012 ጀምሮ በተካሄዱ ጦርነቶች ከ40 በላይ ሆስፒታሎች እና 453 የጤና ተቋማት ወድመዋል
በክልሉ በሚደረገው ውግያ የአለም አቀፍ ህጎች አለመከበራቸው የሰብአዊ ቀውሱን እያባባሰው መሆኑን የአማራ ክልል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ይፋ አድርጓል
በአማራ ክልል 15 ሺህ ንጹሀን ለሞት፣ ለአካል ጉዳትና አስገድዶ መድፈር መጋለጣቸውን የአማራ ክልል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ይፋ አድርጓል።
በክልሉ ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ በቀጠሉ ግጭት እና ጦርነቶች ንጹሀን ዜጎች በሚጠቀሙባቸው ትምህርት ቤት የጤና ተቋማት እና ሌሎችም መሰረታዊ የማህበረሰብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ጉዳት ማድረሱ ተነግሯል፡፡
የአማራ ክልል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ፎረም ክልሉ ባስተናገዳቸው እና እያስተናገዳቸው በሚገኙ ግጭቶች በማህበራዊ መገልገያ ተቋማት በተለይም በጤናው ዘርፍ ስላደረስው ጉዳት ጥናት አስጠንቷል፡፡
ክልሉ በተለያዩ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ የህብረተሰብ ጤና እክሎችን እያስተናገደ ነው የሚለው ጥናት ከግጭት ጋር በተያያዙ ቀውሶች ባለፉት አራት አመታት ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከ3 ሚሊየን 388 ሺህ በላይ ሰዎች ወደ ክልሉ መፈናቀላቸውን ጠቅሷል፡፡
በክልሉ ከሚያዚያ 2015 ጀምሮ እስከ መስከረም አጋማሽ 2017 ድረስ ብቻ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግስት ሀይሎች መካከል እየተካሄደ በሚገኘው ውግያ 15 ሺህ ንጹሀን ሞት ፣ የአካል ጉዳት ፣ የአስገድዶ መድፈር እና የአዕምሮ ህመም ሰለባ ሁነዋል፡፡
አል ዐይን አማረኛ ከጥናቱ ባገኝው መረጃ መሰረት ከ2012 ጀምሮ በቀጠሉ ግጭቶች በክልሉ ከሚገኙ 100 የመንግስት ሆስፒታሎች ውስጥ 40 ያህሉ ወድመዋል፡፡
917 የጤና ጣብያዎች የነበሩት ክልሉ በአሁኑ ወቅት 453 የሚሆኑትን በጦርነት ወድመውበታል፡፡
በፋኖ ታጣቀዊዎች እና በመንግስት ሀይሎች ጦርነት ከተጀመረበት 2015 ጀምሮ እስከ ጥር 2016 ድረስ ብቻ ሁለት የዞን ጤና መምሪያዎችን ጨምሮ 969 የጤና ተቋማት ፣ 62 የወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤቶች፣ 25 ሆስፒታሎች፣ 198 ጤና ጣቢያዎች እና 682 ጤና ኬላዎች ወድመዋል ወይም ተዘርፈዋል።
የአማራ ክልል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም አስጠናሁት ባለው ጥናት በጦርነቶች ጉዳት ከደረሰባቸው የህክምና ማዕከላት መካከል ተጠግነው ወይም ድጋሚ ተገንብተው ስራ የጀመሩት 5 በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው፡፡
በዚህ የተነሳም የአዕምሮ ህመምን ጨምሮ ተላላፊ በሽታዎች እና ወረርሽኞች ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ እንደሚገኝ በጥናቱ ላይ ተመላክቷል፡፡
ከነዚህ መካከል በ2016 ዓም 1.5 ሚሊየን የወባ ተጠቂዎችን አስመዝግቦ የነበረው ክልሉ በ2017 ከ856 ሺህ በላይ ተጠቂዎች የሚገኙበት ሲሆን በዚሁ አመት አራት ወራት ውስጥ ብቻ በወባ ምክንያት 40 ሞት ተመዝግቧል፡፡
ኮሌራን በተመለከተ ከ13 ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው ሲያዙ 217 የሚሆኑት ደግሞ ህይወታቸው አልፏል፤ በተጨማሪም ከ21 ሺህ የሚሻገሩ የአዕምሮ ታማሚዎች በክልሉ ይገኛሉ፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ዋና ጸሐፊ ዶክተር ተፈራ መላኩ ከአል ዐይን ጋር በነበራቸው ቆይታ በክልሉ የተካሄዱ እና አሁንም የቀጠሉ ግጭቶች አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ህጎችን ባለማክበራቸው የክልሉን የሰብአዊ ቀውስ እያባባሰው ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እንደ ዋና ጸሀፊው ገለጻ በግጭቶቹ ጉዳት ከሚደርስባቸው የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ባለፈ በተቋማቱ ውስጥ የሚሰሩ የህክምና ባለሙያዎችም የጥቃቱ ሰለባ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡
ለአብነትም በክልሉ 1 ሺህ 116 የጤና ባለሙያዎች ለሞት ፣ መፈናቀል እና ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለመዘዋወር ተዳርገዋል፡፡
ዶክተር ተፈራ እንደሚሉት “በክልሉ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች በሁለቱም ተዋጊ ወገኖች ጫና ይደርስባቸዋል፤ በዚህ ምክንያት የጤና ባለሙያዎች እጅግ በጣም አስጨናቂ ሁኔታዎች፣ ስነ ልቦናዊ ቀውስ እንዲሁም ከፍተኛ የደህንነት ስጋትን እየተጋፈጡ ነው፡፡”
ሌላው ለክልሉ የጤና ስርአት አስቸጋሪ ሁኔታን ፈጥሯል የሚባለው በክልሉ እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት የመንገድ መዝጋት እና የእንቅስቃሴ ገደብ አስፈላጊ መድኃኒቶችን፣ የሕክምና መሣሪያዎችን እና አቅርቦቶችን ለማጓጓዝ በከፍተኛ ደረጃ እንቅፋት ሆኗል፡፡
ከባህር ዳር ከተማ እስከ ዞንና ወረዳዎች እና የጤና ተቋማት የሚደረግ የህክምና ግብአቶች ስርጭትን ማስተጓጎል የትኛውም አካል ቢፈጽመው ከዓለም አቀፍ ህግ ጋር የሚቃረን እና የሰብአዊነት መርሆዎችን የሚጥስ ስለመሆኑ ዶክተር ተፈራ ያስረዳሉ፡፡
የኢንተርኔት፣ የስልክ እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥ በተጎዱ ማሕበረሰቦች ትክክለኛ የጤና ፍላጎት ላይ በመመስረት መደበኛ የጤና እና የሎጂስቲክስ መረጃዎችን ማግኘት ላይ በአጠቃላይ በጤና መረጃ አስተዳደር ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።
የፎረሙ ዋና ጸሀፊ ዶክተር ተፈራ አጠቃላይ አሁናዊ ሁኔታዎችን አስመልክቶ ለአል ዐይን በሰጡት ማብራርያ “እኛ ማንንም የመውቀስ አላማ የለንም ግን ደግሞ አለምአቀፋዊ ህጎች እንዲከበሩ እና በጦርነቱ የሚደርሱ ጉዳቶች እንዲቀንሱ እንፈልጋለን፤ ጤና የመኖር እና የአለመኖር ጉዳይ ስለሆነ ቅድሚያ ሰጠነው እንጂ ትምህርትን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች ላይ እየደረሱ የሚገኙ ጉዳቶች አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ” ብለዋል::
የአማራ ክልል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም በክልሉ የተከሰቱ ግጭቶች በጤናው ዘርፍ ላይ ያሳደሩት ጫና፤ ይህንን ተከትሎ የተፈጠሩ ተብአዊ ቀውሶችን በተመለከተ ያስጠናውን ጥናት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጄንሲዎች ፣ የአለም ጤና ድርጅት ፣ የሰብአዊና የረድኤት ድርጅቶች እንዲሁም ኢምባሲዎች በተገኙበት አቅርቧል፡፡
የጥናቱን አላማ በተመለከተ ዶክተር ተፈራ ሲያስረዱ “ጥናቱ አጠቃላይ የክልሉን የሰብአዊ ሁኔታዎች አለም አቀፉ ማሕበረሰብ እንዲረዳ ማስቻል አላማው አድርጓል፤ ሁለተኛው ግጭቱ እያደረሰ ከሚገኘው ጉዳት አንጻር ከሰብአዊ እና ከጤና ጋር በተያያዘ የሚሰሩ ድርጅቶች ክልሉን መደገፍ በሚችሉበት ሁኔታ ዙርያ ጥናቱ የራሱን ምክረ ሀሳቦች አስቀምጧል፤ ሌላው እና ዋነኛው ደግሞ በግጭቱ እየተሳተፉ የሚገኙ አካላት አለም አቀፍ ህጎችን እና የሰብአዊ መብቶችን እንዲያከብሩ አለም አቀፉ ማሕበረሰብ ጫና እንዲያሳድር ለመጠየቅ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡