የከተሞች ልማት የአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂዎችን ያማከለ መሆን ይገባዋል - የኮፕ28 ፕሬዝዳንት
በዱባዩ ጉባኤ ከ450 በላይ የከተማ መሪዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው
የአካባቢ ጥበቃ፣ የቤቶችና ከተማ ልማትና ሚኒስትሮችም በቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ መክረው ከስምምነት ላይ ደርሰዋል
የከተሞች ልማት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን ማዕከል ባደረገ መልኩ ሊካሄዱ እንደሚገባ የኮፕ28 ጉባኤ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሱልጣን አል ጀበር አሳሰቡ።
የኤምሬትስ የኢንዱስትሪና ቴክኖሊጂ ሚኒስትር እና የኮፕ28 ጉባኤ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሱልጣን አልጀበር የአየር ንብረት ለውጥ እና የከተሞች ደህንነት ላይ ባተኮረ ውይይት ላይ ንግግር አድርገዋል።
ዶክተር ሱልጣን በዚሁ ወቅት ከተሞች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ጉዳት ለሚደርስባቸው ነዋሪዎቻቸው ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
የከተሞች መሪዎች እና ባለሙያዎች በአየር ንብረት ለውጥ የሚጉዱ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ እንዲሰሩም ነው የጠየቁት።
በኮፕ28 ጉባኤ ከመላው አለም ከ450 በላይ የከተሞች አስተዳዳሪዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
ከ40 በላይ የአካባቢ ጥበቃ፣ የቤቶችና የከተማ ልማት ሚኒስትሮችም በጉባኤው ላይ በመሳተፍ ቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ መክረዋል።
ሚኒስትሮቹ ባለ10 ነጥብ መሰረታዊ እቅድ ላይም የተስማሙ ሲሆን፥ የከተሞች መሪዎች በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በሚተላለፉ ውሳኔዎች ቀጥተኛ ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል።
ከተሞች የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ በሚከናወኑ ተግባራት በቂ የፋይናንስ ድጋፍ ማግኘት እንደሚገባቸውም ተስማምተዋል።
28ኛው የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ዛሬ ስምንተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን ታህሳስ 2 2016 ይጠናቀቃል።