የስብ መጠናቸው ከፍ ያለ ምግቦችና የውሃ ጥም የሚያስከትሉ ትኩስ መጠጦችን ከመውሰድ መቆጠብ ጾሙን በብርታት ለመጨረስ ያግዛል ተብሏል
ጾም ለሰው ልጆች ያለው መንፈሳዊ ብሎም አለማዊ በረከት በተደጋጋሚ ተጠቅሷል።
የተለያዩ ጥናቶች ጾም ሰውነታችን መርዛማ የሆኑ ነገሮችን በተፈጥሯዊ መንገድ እንዲያስወግድ እንደሚረዳ አመላክተዋል።
እናም በረመዳን ወር በስሁር ወቅት የምግብ ጠረጼዛችን ላይ የሚቀርቡ ምግቦችና መጠጦች ጥንቃቄ ሊደረግባቸው እንደሚገባ ነው ባለሙያዎች የሚመክሩት።
በረመዳን የጾም ወቅት በስሁር (ቁርስ) ከተመገብናቸው ሰውነታችን ይጎዳሉ የተባሉ የምግብ አይነቶች ቀጥለው ቀርበዋል፦
1. የተጠበሱና ቅባታማ ምግቦች
አይብ፣ ቅቤ፣ የተጠባበሱ እና ቅባታማ ምግቦች በስሁር ወቅት አይመከሩም፤ ምንም እንኳን ጣፋጭ ቢሆኑም የምግብ መፈጨት ሂደት በማስተጓጎል ሰውነትን ያደክማሉ። ስብ ለሰውነታችን ወሳኝ ቢሆንም የምንጠቀመው መጠን መብዛትና የስብ አይነቱም ጤናማ አለመሆን በረመዳን ጾም ክብደት ለመጨመር ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። የልብ ቃር እና ሌሎች እክሎችም በእነዚህ ምግቦች ምክንያት ተከስቶ ጾሙን ሊያውክ ይችላል ነው የሚሉት የህክምና ባለሙያዎች።
2. ስኳር የበዛባቸው ጣፋጭ ምግቦች
ኬክ፣ ፓስቲ፣ ስኳር የበዛባቸው የተጠባበሱ ምግቦች ወዲያውኑ የመጥገብ ስሜት እንዲሰማን ቢያደርጉም የካርቦሃይድሬት መጠናቸው አነስተኛ በመሆኑ ለረጅም ስአት ያለድካም ለመቆየት አያስችሉም።
3. ጨዋማ ምግቦች
በሰውነታችን ውስጥ ያለ የሶዲየም መጠን አለመመጣጠን የውሃ ጥምን ያስከትላል። በመሆኑም በስሁር ወቅት ጨው የበዛባቸውንና የውሃ ጥም የሚያስከትሉ ምግቦችን አለመውሰድ ተገቢ ነው።
4. የካፌይን ይዘት ያላቸው መጠጦች
ቡና፣ አረንጓዴ ሻይ እና ሌሎች ከፍተኛ የካፌይን ይዘት ያላቸውን ትኩስ መጠጦች በስሁር ወቅት መጠጣት የውሃ ጥም ከማስከተሉ ባሻገር እንቅልፍ ማጣትንም ያመጣል። በመሆኑም የካፌይን ይዘታቸው ከፍ ያሉ ትኩስ መጠጦችን በስሁር ወቅት መጠጣት አይመከረም ተብሏል።