ታዋቂው የእግር ኳስ አሰልጣኝ ኤሪክሰን ህይወት አለፈ
ስዊድናዊ አሰልጣኝ ኤሪክሰን ማንችስተር ሲቲን ጨምሮ በርካታ ክለቦችን እና ብሔራዊ ቡድኖችን አሰልጥነዋል
የ76 ዓመቱ ኤሪክሰን በጣፊያ ካንሰር ህመም ተጠቅተው ህይወታቸው አልፏል
ታዋቂው የእግር ኳስ አሰልጣኝ ኤሪክሰን ህይወት አለፈ።
በርካታ የእግር ኳስ ክለቦችን እና ብሔራዊ ቡድኖችን በማሰልጠን የሚታወቁት ስቨን ጎራን ኤሪክሰን በጣፊያ ካንሰር መጠቃታቸውን ለህዝብ ይፋ አድርገው ነበር፡፡
እንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንን ያሰለጠኑት ስዊድናዊው ኤሪክሰን ባጋጠማቸው የካንሰር ህመም ምክንያት ከአንድ ዓመት ያነሰ ጊዜ በህይወት እንደሚኖሩም በወቅቱ ገልጸውም ነበር፡፡
አሰልጣኙ በጣፊያ ካንሰር መጠቃታቸውን ዘግይተው ማወቃቸው ህክምናውን እንዳከበደባቸው ተነግሯል።
ኤሪክሰን ከአንድ ዓመት በፊት ስለጤናቸው በተናገሩበት ወቅት እንዳሉት የጣፊያ ካንሰር በቶሎ ከማይድኑ የካንሰር አይነቶች ውስጥ እንደሆነ እና በህይወት የምቆየው ቢበዛ አንድ ዓመት ነው ሲሉም ይህንንም እሳቸው እና ቤተሰባቸው እንደተቀበለው ለሚዲያዎች ተናግረው ነበር።
አሰልጣኙ ከእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን በተጨማሪም የእንግሊዙ ማንችስተር ሲቲ፣ የጣልያኑን ላዚዮ፣ ከፖርቹጋሉ ቤነፊካ እንዲሁም ከስዊድኑ ጎተንበርግ ክለቦችን አሰልጥነው ዋንጫዎችን ማሸነፍ ችለዋል፡፡
በህይወት ዘመናቸው ምን ማድረግ ይፈልጉ ነበር ተብለው ሲጠየቁም "ሊቨርፑልን ማሰልጠን ህልሜ ነበር" ሲሉ ባንድ ወቅት በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ላይ መናገራቸው አይዘነጋም።