በኦሎምፒክ የእግር ኳስ ግጥሚያ ግብጽ እና ፈረንሳይ ወደ ግማሽ ፍጻሜው አለፉ
ትላንት ምሽት በነበረው ጨዋታ የዘንድሮ ኮፓ አሜሪካ አሸናፊ አርጄንቲና በፈረንሳይ ተሸንፋ ከውድድሩ ወጥታለች
በምሽቱ ጨዋታ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች እና ተጨዋቾች ለጥል ሲጋበዙ ታይተዋል
በኦሎምፒክ የእግር ኳስ ግጥሚያ ግብጽ እና ፈረንሳይ ወደ ግማሽ ፍጻሜው አለፉ።
ፈረንሳይ እና አርጄንቲና ባደረጉት የኦሎምፒክ የእግር ኳስ ግጥሚያ አዘጋጇ ሀገር 1ለ0 በሆነ ውጤት የ16 ጊዜ የኮፓ አሜሪካ አሸናፊዋን አርጄንቲና መርታት ችላለች፡፡
የክሪስታል ፓላሱ አጠቂ ጄን ፍሊፕስ በ50ኛው ደቂቃ ከማአዘን የተሸገረለትን ኳስ ወደ ግብ በመቀየር ሀገሩ ወደ ቀጣይ ዙር አንድትሻገር አስችሏል፡፡
በቅርቡ የኮፓ አሜሪካ ዋንጫ ያሸነፉት አርጄንቲናዎች ከዋንጫ ስነስርአቱ በኋላ የፈረንሳይ ጥቁር ተጫዋቾችን የሚያጥላላ የዘረኝነት ጭፈራ መጨፈራቸውን ተከትሎ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በውጥረት የተሞላ ነበር፡፡
የፈረንሳይ ደጋፊዎችም በጨዋታው ጅማሪ የአርጄንቲና መዝሙር በሚዘመርበት ወቅት የረብሻ ጩኸት በማሰማት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡
የጨዋታው መጨረሻ ፊሽካ ከተሰማ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኝ እና ተጨዋቾች በሜዳ ውስጥ ሲተናነቁ ተስተውለዋል፡፡
በ2022 ኦሎምፒክ በመለያ ምት ፈረንሳዮችን ያሸነፉት አርጄንቲናዎች የአለም ዋንጫ እና የኦሎምፒክ ሜዳሊያን በማንሳት ከጣሊያን ቀጥሎ ሌላኛው ሀገር ለመሆን እቅድ ይዘው ነበር፡፡
የፈረንሳይ የእግር ኳስ ቡድን በኦሎምፒክ ለመጨረሻ ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኝው በ1984ቱ ኦሎምፒክ ነበር፡፡
ፓራጓይን በመለያ ምት 5ለ4 በሆነ ውጤት ያሸነፈው የግብጽ ብሄራዊ ቡድን በመጭው ሰኞ ለፍጻሜ ለማለፍ ከአዘጋጇ ሀገር ጋር ይገጥማል፡፡
ቀሪ ሁለት የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚዮች የስፔን እና ሞሮኮ ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡
ጃፓንን 3ለ0 በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜ የተሻገረችው የዘንድሮ የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊዋ ስፔን ለወርቅ ሜዳሊያ ቅድመ ግምት ከተሰጣቸው ቡድኖች መካከል አንዷ ናት፡፡
በፈረንሳይ ሊዮን በተደረገው ጨዋታ ፍርሚን ሎፔዝ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል፡፡
የአውሮፓ ዋንጫ ያሸነፈው የስፔን ብሄራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ የነበረው የባርሴሎናው አማካይ ሎፔዝ በቡድኑ ጠንካራ አቋም እያሳዩ ከሚገኙ ተጨዋቾች መካከል ይጠቀሳል፡፡
በውድድሩ ለመጀመርያ ጊዜ የመጨረሻ አራት ውስጥ የተካተቱት ሞሮኮዎች አሜሪካን 4 ለዜሮ አሸንፈዋል፡፡
ከውድድሩ ጅማሮ ጀምሮ ጥሩ አቋም እያሳዩ የሚገኙት ሞሮኮዎች ከግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚያቸው ስፔን ጠንካራ ፉክክር የሚጠብቃቸው ይሆናል፡፡
16 ቡድኖች በተመደቡበት ከ23 አመት በታች ተጫዋቾች የሚሳተፉበት የኦሎምፒክ የእግርኳስ ግጥሚያ ላይ አፍሪካ በ4 ቡድኖች ተወክላ የነበረ ሲሆን ሁለት ቡድኖች ግማሽ ፍጻሜውን መቀላቀል ችለዋል፡፡