ቻትጂፒቲን ጨምሮ ሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚጠቀሙ ቴክኖሎጂዎች በፍርድ ቤቶች ለሚቀርቡ ክሶች የሚሰጡ ምላሾችን በማቅረብ ላይ ናቸው
የሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ለደንበኞቹ ህጋዊ ምክርን የሚሰጠው የአለማችን የመጀመሪያው የሮቦት ጠበቃ ክስ ቀርቦበታል።
ዱኖትፔይ በተሰኘ የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያ የተሰራው ሮቦት ህጋዊ የጥብቅና ፈቃድ የለውም የሚል ክስ ነው የቀረበበት።
መቀመጫውን ቺካጎ ባደረገው ኢዲልሰን የህግ አማካሪ ተቋም የቀረበው ክስ የሮቦት ጠበቃው “ሮቦት ወይም የህግ ተቋም አይደለም፤ እንደ ሰው የሚቆም ጠበቃ እስከሆነ ድረስ ህጋዊ ፈቃድ ያስፈልገዋል” ይላል።
ክሱን ጆናታን ፋሪዲያን የተባለ ግለሰብ በኢዲልሰን በኩል ለሳንፍራንሲስኮ አካባቢ ፍርድ ቤት ያቀረበ ሲሆን፥ ፍርድ ቤቱ ክሱን በድረገጹ ላይ አስፍሮታል።
ፋሪዲያን የዱኖትፔይ ሮቦት ጠበቃን በመጠቅም ለፍርድ ቤት መልስ የሚሆን ደብዳቤ እንዲጽፍልኝ ባደርግም ውጤቱን የማያስደስት ሆኖ አግኝቼዋለሁ ማለቱንም ነው ሬውተርስ የዘገበው።
የዱኖትፔይ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጆሽዋ ብሮውደር በትዊተር ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ ግን የፋሪዲያንን ክስ መሰረተ ቢስ ውንጀላ ነው በሚል ተቃውሟል።
ክሱንም የሮቦት ጠበቃው ስራ ያቀዘቅዝብኛል ብሎ ያመነው ኢዲልሰን የተሰኘው ኩባንያ ያቀነባበረው ሴራ አድርገው ተመልክተውታል።
የኢዲልሰን የህግ አማካሪ ተቋም መስራች ጄይ ኢዲልሰን ግን ዱኖትፔይ የበርካታ ሰዎችን መረጃ መዝረፉንና የሮቦት ጠበቃው ስራም በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው ነው ብለዋል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለህግ ማማከር ስራዎች የመጠቀም ጉዳይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትኩረትን እየሳበ ነው።
ቻትጂፒቲን ጨምሮ የተለያዩ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሚጠቀሙ መተግበሪያዎች ለትራፊክ እና ሌሎች ክሶች ፈጣን ምላሾችን በመስጠት ላይ ናቸው።
በፈረንጆቹ 2015 የተመሰረተው ዱኖትፔይ ከፍጥነት ገደብ በላይ በማሽከርከር የተከሰሰ ደንበኛውን ነጻ ለማውጣት የሕግ ምክር በመለገስ ስራ ይጀምራል ቢባልም ራሱ ክስ ቀርቦበታል።
ሮቦት ጠበቃው በተከሳሹ ስማርት ስልክ ላይ በመሆን ከዓቃቤ ሕግ የሚቀርበውን ክስ እና አስተያየት በመስማት ደንበኛው በክርክሩ ወቅት ምን መመለስ እንዳለበት መመሪያ መስጠት የሚችል ነው።
በአሜሪካ በርካታ ፍርድ ቤቶች ተከሳሾች ጆሮ ላይ የሚደረጉና በብሉቱዝ የሚተሳሰሩ ማዳመጫዎችን መጠቀም መከልከላቸው የዱኖትፔይ ሮቦት ጠበቃው ፍርድ ቤት የመታየቱን ነገር አጠራጣሪ ያደርገዋል።