የብራዚላዊው የእግር ኳስ ንጉስ ፔሌ ህልፈትን ተከትሎ የሀገራት መሪዎች ምን አሉ?
“እንደ እሱ ያለ 10 ቁጥር ተጫዋች በዚህች ምድር ላይ የለም”- የብራዚል ፕሬዝዳንት ሉላ
“ሜሲ፣ ሮናዶ፣ ቤካም ከመፈጠራቸው በፊት ፔሌ ነበረ”- ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን
ብራዚላዊው የእግር ኳስ ንጉስ ፔሌ ትናንተ ምሽት በ82 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋች ፔሌ በካንሰር ህመም ምክንያት ሆስፒታል ገብቶ ህክምና ሲከታተል የቆየ ሲሆን፤ ትናንት ምሽት የህልፈቱ ዜና ተሰምቷል።
የህልፈቱን ዜና ተከትሎም የዓለማችን ሀገራት መሪዎች፣ የእግር ኳስ ተጫዋቾች እንዲሁም ሌሎች ታዋቂ ሰዎች በአንድ ድምጽ ሀዘናቸወን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።
የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ሉላ ዳሲልቫ
“ወጣቱ የብራዚል ትውልድ ያላገኘውን ዕድል እኔ አግኝቻለሁ፤ ምክንያቱም “ፔሌ በፓኬምቡ እና ሞሩምቢ ሲጫወት በአካል ተገኝቼ በቀጥታ ተመልክቻለሁ፤ ፔሌ ኳስ ሲይዝ ሁል ጊዜ ልዩ የሆነ ነገር ይሰራ ነበር ይህም ብዙ ጊዜ ወደ ጎል ይለወጣል” ብለዋል።
ፔሌ ዛሬ ትቶን ሄዷል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በሰማይ ቤት በሳንቶስ የእግር ኳስ ክለብ ዋና አጋሩ እና ጓደኛው ከሆነው ኩቲኒሆ ጋር ለመገናኘት ወደ ሰማይ ሄዷል፤ ፔሌ አሁን የብዙ ዘላለማዊ ኮከቦች ከሆኑት ዲዲ፣ ጋሪንቻ፣ ኒልተን ሳንቶስ፣ ሶቅራጥስ እና ማራዶናን ተቀላቅሏል ሲሉም ገልጸዋል።
“አንድ ነገር ግን እርገጠኛ መሆን እችላለ”ሁ ያሉት ፕሬዝዳንት ሉላ ዳሲልቫ፤ “እንደ እሱ ያለ 10 ቁጥር ማሊያ ለባሽ ተጫዋች በዚህች ምድር ላይ የለም” ብለዋል።
ብራዚል የእውቁን የእግር ኳስ ተጫዋች ህልፈት ተከትሎ ሶስት ብሄራዊ የሀዘን ቀናት ማወጇም ተሰምቷል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን
“ሜሲ፣ ሮናልዶ፣ ቤክሃም ከመፈጠራቸው በፊት ፔሌ ነበረ” ያሉት ፕሬዝዳንት ባይደን “በ1958 በ17 ዓመቱ የመጀመሪያውን የዓለም ዋንጫ ከብራዚል ጋር አነሳ፤ ይህም በእድሜ ትንሹ የዓለም ዋንጫን ያነሳ ብቸኛ ተጫዋች አደረገው” ብለዋል።
በ1962 እና በ1970 ፔሌ ከሀገሩ ብራዚል ጋር በመሆን ሁለት ዋንጫዎችን ማንሳቱንም ያወሱት ፕሬዝዳንት ባይደን፤ ይህም ፔሌ ሶስት የዓለም ዋንጫዎችን ማንሳት የቻለ ብቸኛ የዓለማችን ተጫዋች አድርጎታል ብለዋል።
“ፔሌ ዓለምን አንድ በሚያደርገው ስፖርት ውስጥ ደማቅ ታሪክ የጻፈ ነው” ያሉት ባይደን ለመላው እግር ኳስ አፍቃሪ እና ለብራዚላውያን ሀዘናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ መንግስትም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል በእውቁ የእግር ኳስ ተጫዋች ህልፈትን ተከትሎ ብራዚል ፌደሬሽን ሪፐብሊክ መንግስት፣ የብራዚል ህዝብ እና የእግር ኳስ ማህበረሰቡን የተሰማውን ሀዘን ገልጿል።
የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ
“ፔሌ ቆንጆ የእግር ኳስ ጨዋታ ከተጫወቱት ታላላቅ ተጫዋቾች አንዱ ነበር”። እንዲሁም በዓለም ላይ በጣም ከሚታወቁ አትሌቶች አንዱ እንደመሆኑ መጠን ሰዎችን አንድ ላይ ለማምጣት የስፖርትን ኃይል መረዳት የቻለ ነበር ብለዋል።
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን ጨመሮ ሌሎች የዓለማ ሀገራት መሪዎች በእውቁ የእግር ኳስ ተጨዋች ፔሌ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።
በፈረንጆቹ በ 1940 የተወለደው ፔሌ እግር ኳስ ገና በልጅነቱ በአስራ አምስት ዓመቱ በሳንቶስ ክለብ በመጫወት መጀመሩ ይታወቃል።
በአራት የዓለም ዋጫዎች ላይ መጫወት የቻለው ፔሌ ከብራዚል ብሔራዊ ቡድን ጋር ሶሰት የዓለም ዋንጫዎችን ማንሳት የቻለ ድንቅ የእግር ኳስ ተጫዋች መሆኑ ይታወቃል።
ፔሌ በሳንቶስ ቆይታውም ከክለቡ ጋር ስድስት የሊግ ዋንጫ ፣ ሁለት ኮፓ ሊቤርታዶሬስ እና ሁለት ኢንተር ኮንቲኔንታል ዋንጫዎችን ማንሳት ችሏል
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ አካለ ፊፋ ፔሌን ታላቁ ተጫዋች ሲል የሚጠራው ሲሆን፤ በፈረንጆቹ 2000 የአለም አቀፍ እግር ኳስ እና ታሪክ የምትዓመቱ የዓለማችን ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን መቀዳጀቱም ይታወቃል።
ፔሌ በእግር ኳ ዘመኑ 1 ሺህ 228 ግቦችን ከመረብ ያሳረፈ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 77ቱ ለሀገሩ ብራዚል ያስቆጠራቸው ናቸው።