ምንጣሮው በ17 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ይከናወናል ተብሏል
ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 3ኛ ዙር ሙሌት የሚሆን የደን ምንጣሮ ስራ ሊጀመር ነው፡፡
ምንጣሮው ለ3ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን ክረምት ከመግባቱ አስቀድሞ ለማጠናቀቅ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡
ይህን የተመለከተ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ውይይት ዛሬ ሐሙስ ጥር 5 ቀን 2014 ዓ/ም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ በ2014 ዓ.ም በግድቡ 3ኛ ዙር ሙሌት የሚያዘው ውሃ በሚተኛበት 17 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚገኘውን ደን ክረምት ከመግባቱ በፊት መንጥሮ ለማጠናቀቅ የሚያስችል ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ምንጣሮውን ከክረምቱ ቀድሞ ማከናወኑ ፋይዳው የጎላ መሆኑን በመጠቆም ለዚህ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ያደርጋል ብለዋል፡፡
በጀትን ጨምሮ ለምንጣሮው የሚያስፈልገውን ስራ በተያዘው ጥር ወር በማጠናቀቅ ከየካቲት 01/2014 ዓ.ም ጀምሮ ሥራውን መጀመር እንደሚገባም ነው አቶ አሻድሊ የገለጹት፡፡
ይመነጠራል ከተባለውና 17 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከሚገኘው ደን ውስጥ ከ10 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው በ250 ኢንተርፕራይዞች በታቀፉ ከ5 ሺህ በላይ የክልሉ ወጣቶች የሚመነጠር ነው እንደ ክልሉ የቴክኒክ ሙያ እና ሥራ ዕድል ፈጠራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በሽር አብዱራሂም ገለጻ፡፡
ዝግጅቶችን በቶሎ አጠናቆ ምንጣሮውን በአንድ ወር ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዷልም ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡
በዝግጅት ስራውም የጸጥታ፣ የጤና፣ የውኃ አቅርቦት፣ የመንገድ ከፈታ እና ሌሎች ሥራዎች እንደሚከናወኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የጸጥታ ስጋት ይኖርባቸዋል ተብሎ በሚታሰቡ አካባቢዎች ደግሞ በመከላከያ ሠራዊት እገዛ ምንጣሮው እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
በውይይቱ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢ/ር አይሻ መሃመድን እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች መገኘታቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
2ኛ ዙር ሙሌቱን ባሳለፍነው ክረምት ሀምሌ 12 ቀን 2013 ዓ/ም ያጠናቀቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በቅርቡ ኃይል ማመንጨት ይጀምራል መባሉ የሚታወስ ነው፡፡