ግድብ አሁን ባለው የግንባታ ቁመት 400 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫል-የግድቡ ተደራረዳሪ
ግብጽና ሱዳን የግድቡን ጉዳይ የደህንነት ስጋት ነው በማለት ወደ ተመድ ወስደውታል
የተመድ የጸጥታው ም/ቤት የግድቡ ድርድር በአፍሪካ ህብረት ስር ይካሄድ የሚለውን የኢትዮጵያን አቋም ደግፎታል
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አሁን ባለው የግንባታ ቁመት 400 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት እንደሚችል የህዳሴ ግድብ ተደራዳሪና የባለሙያዎች ቡድን ሰብሳቢ አስታወቁ፡፡
ሰብሳቢው ኢ/ር ጌዴዮን አስፋው ለኢቲቪ እንደገለጹት የሁለቱ ተርባይኖች ሙሉ የማመንጨት አቅም 750 ሜጋ ዋት ሲሆን አሁን ግድቡ ባለው ቁመት ግን 400 ሜጋ ዋት ማመንጨት ይችላል፡፡ ሁለቱ ተርባይኖች 24 ሰዓት ሰርተው፤ ዓመቱን ሙሉ ሰርተው ጥሩ ውኃ ካገኙ የሚያመነጩትና አሁን ባለው የውኃ ቁመት ማመንጨት የሚችሉት ኃይል እንደሚለያይ ኢ/ር ጌዲዮን ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሰረት ሁለቱ ተርባዮኖች አሁን ባለው የውኃ ቁመት 400 ሜጋ ዋት ሊደርስ ይችላል፡፡ ሁለቱ ተርባይኖች የሚያመነጩት ኃይል ማለት ተከዜና ሌሎች ግድቦች ከሚያመነጩት ኃይል ከፍ ያለ መሆኑን ኢ/ር ጌዲን ተናግረዋል፡፡
ከሁለቱ ተርባይኖች ጀምሮ በሚቀጥሉት ዓመታት ሃይል ማመንጨቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ በውሃው ከፍታና መጠን እየጨመረ ይሄዳል ያሉት የሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪና የባለሙያዎች ቡድን ሰብሳቢ ኢ/ር ጌዴዮን፤ ከሕዳሴ ግድቡ የሚመነጨው ኃይል ወዲያውኑ ወደ ማዕከላዊ ቋት ማከፋፈል የሚያስችለው ከሆለታ እስከ ሕዳሴ ግድብ ያለው 650 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ዋና ማስተላለፊያ መስመሩ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውኃ ሙሌትን ተከትሎ ወደ ሥራ የሚገቡ ሁለት ተርባይኖች በሙሉ አቅማቸው ካመረቱ እስከ 750 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይል እንደሚያመርቱ የተገለጸ ሲሆን ይህም አሁን ሀገሪቱ ያላት ኃይል የማመንጨት አቅም በእጅጉ ያሳድገዋል ነው የተባለው፡፡
ኢትዮጵያ አሁን በሰዓት 13 ሺ ጊጋ ዋት ኃይልን ማመንጨት ትችላለች፡፡ የሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ኮሚቴ አባል ዶ/ር በለጠ ብርሃኑ፤ ሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅና ምርት መስጠት በሚጀምርበት ጊዜ በሰዓት 15 ሺ 700 ጊጋ ዋት ማመንጨት እንደሚችልና ይህም ዛሬ ባለው የኤሌክትሪክ ሬት 1 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
ሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ የጣና ኃይቅን እጥፍ የሚሆን ሐይቅ የሚኖረው ሲሆን በአጠቃላይ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ እንደሚይዝ ይጠበቃል፡፡ ግድቡ መገንባት ከመጀመሩ በፊትና በኋላ በተለየ ሁኔታ ግብፅ፤ አንዳንድ ጊዜ በተለይ በቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ሱዳን ተቃውሞዎችን እያሰሙ ናቸው፡፡ ከተቃውሞ ባለፈም ጉዳዩ ወደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ም/ቤት መውሰዳቸው የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው፡፡
በዚህም መሰረት የተመድ የጸጥታው ም/ቤት ባለፈው ሳምንት በኒውዮርክ ባደረገው ስብሰባ በግድቡ ዙሪያ ያለው አለመግባት በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር መፈታት እንዳለባቸው ቋሚና ተለዋጭ የጸጥታው ምክር ቤት አባላት መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡
ም/ቤቱ በጉዳይ ላይ ጣልቃ ሊገባ የቻለው፣ ግብጽና ሱዳን የግድቡ ጉዳይ የዓለም አቀፍ የደህንነት ስጋት እንደሆነ ሃሳብ በማቅረባቸው ነው፡፡ ከኒውዮርክ ስብሰባ በኋላ የግብጽ እና ሱዳን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ ቤልጅየም እና ሩሲያ ማቅናታቸው ታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ፣ግብጽና ሱዳን ከግድቡ መጀመር አንስቶ ውዝግብ ላይ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ የምትገነባው ግድብ ከድህነት መውጫ የሚሆን የሃይል ማመንጫ መሆኑንና በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉልህ ተጽዕኖ እንደማያደርስ በተደጋጋሚ ገልጻለች፡፡ ግብጽና ሱዳን በአንጻሩ በግድቡ ላይ የተለያየ ስጋት አላቸው፤በተለይ ግብጽ ታሪካዊ የውሃ ድርሻየ ይቀንሳል የሚል ስጋት ማንሳቷን እስካሁን ቀጥላበታለች፡፡