ግለሰቧ ህጻኑን ያገተችው ተቀጥራ ትሰራ ከነበረችበት ቤት ሲሆን 4 ቀናትን አግታ አቆይታዋለች
ህፃን በማገት 600 ሺህ ብር የጠየቀቺው ተጠርጣሪ ተያዘች
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ታች አርማጭሆ ወረዳ የአሰሪዎቿን የ2 ዓመት ልጅ በማገት የማስለቀቂያ 600 ሺህ ብር የጠየቀችው የቤት ሰራተኛ በቁጥጥር ስር ውላለች፡፡
ሰላም ዋሴ ትሰኛለች የተባለላት ግለሰቧ ህፃን አማኑኤል ስሜነህን ግንቦት 10 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽቱ 3:00 ሰዓት አካባቢ ነው ተቀጥራ ከምትሰራበት ቤት አግታ የወሰደችው፡፡
ተባባሪ ግብረ አበሮች አሏትም ተብሏል፡፡
ህጻኑን ይዛ ከተሰወረች በኋላ ለ4 ያህል ቀናት አግታ አቆይታዋለች፡፡
ለህጻኑ ቤተሰቦች ስልክ በመደወልም 600 ሺህ ብር እንዲከፍሏትና ልጃቸውን እንድትመልስላቸው ትጠይቃለች፡፡
መረጃው የደረሰው የወረዳው የሰላምና ደህንነት ጽህፈት ቤትም ድርጊቱ ከተፈፀመ ጀምሮ በታች አርማጭሆ እና በወገራ ወረዳዎች ስምሪት ማድረጉን አስታውቋል፡፡
በስምሪቱም ባሳለፍነው ቅዳሜ ከጠዋቱ 4 ሰዓት አካባቢ አጋች ሰላም ዋሴ ህፃን አማኑዔልን እንደያዘች በወገራ ወረዳ ግራርጌ ከተባለ የገጠር ቀበሌ በቁጥጥር ስር አውሏታል።
በተሟላ ጤንነት ላይ ይገኛል የተባለውን ህጻን አማኑዔልንም ለቤተሰቦቹ ስለማስረከቡ ነው ያስታወቀው፡፡
በወቅቱ አንድ ግብረ አበሯ በቁጥጥር ስር መዋሉን ለወረዳው መንግስት ኮሙኒኬሽን የተናገሩት አቶ አንተነህ የተባሉት የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ የተያዙት ወንጀለኞች በምርመራ ላይ እንደሆኑ እና ለጊዜው ያልተያዙ ቀሪ 3 ግብረአበሮችን በቁጥጥር ስር አውሎ ለህግ ለማቅረብ ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቅርቡ በዞኑ በሰው ማገት ወንጀል ጥፋተኛ የተባለ ግለሰብ በ11 ዓመት ፅኑ እስራት መቀጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።