ምዝገባውን ያላከናወኑ ህጋዊ እርምጃ ይወሰድባቸዋል ተብሏል
የመንግስት ባለሥልጣናት እስከ ሰኔ 30 ሀብታቸውን እንዲያሳውቁ ተጠየቀ
የፌደራል፣ የአዲስ አበባና ድሬዳዋ አስተዳደሮች እና የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች ሀብታቸውን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2012 ድረስ እንዲያሳውቁ የፌደራል የስነምግባርና የፀረሙስና ኮሚሽን ጠየቀ፡፡
የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎቹ ሀብታቸውን የሚያስመዘግቡት በኮሚሽኑ ቢሮ በአካል በመገኘት ነው፡፡
በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ውስጥ የሀብት ምዝገባ ያላከናወኑ አመራሮች ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸውም ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
የሀብት ማሳወቅ እና ማስመዝገብ አዋጅ አንቀፅ 4 ንዑስ አንቀፅ 1 “ማንኛውም ተሿሚ በራሱና በቤተሰቡ ባለቤትነት ወይም ይዞታ ሥር የሚገኝ ሀብትና የገቢ ምንጮች፣ የማሳወቅና የማስመዝገብ ግዴታ አለበት” ይላል፡፡
አዋጁ በዋናነት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤዎች፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የመከላከያ ሠራዊትና ፖሊስ ተሿሚዎች፣የፌደራል ተቋም ስልጣን ያለው የትኛውም አካል ተሿሚዎች፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባና ምክትል ከንቲባ፣ አፈጉባኤዎችና ሁሉንም የከተማ አስተዳደር፣ የክፍለ ከተማ፣ የወረዳና የቀበሌ ተሿሚዎችን ያካትታል፡፡
በአዋጁ መሠረት ሀብትና የገቢ ምንጫቸውን በወቅቱ የሚያስመዘግቡ የመንግስት ተሿሚዎች ያሉትን ያህል ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢደረግላቸውም ለማስመዝገብ ፍቃደኛ ያልሆኑ አንዳንድ አመራሮች እንዳሉም ነው ኮሚሽኑ የገለጸው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ቀደም የሀብት ማሳወቅ እና ማስመዝገብ ሥርዓትን በአዋጅ ቁጥር 668/2002 አውጥቶ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
ሆኖም እስካሁን ምን ያህል የሥራ ኃላፊዎች ሀብት እንዳሳወቁና እንዳስመዘገቡ ኮሚሽኑ ያለው ነገር የለም፡፡