የአንበጣ መንጋ ክስተት በኢትዮጵያ ለተወሰኑ ጊዜያት ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚችል ትንበያዎች አመለከቱ
መንጋው በአሁኑ ወቅት በ5 የሃገሪቱ ክልሎች ተከስቷል
መንጋውን ለመከላከል 10 አውሮፕላኖች እና 150 የመስክ ተሽከርካሪዎች ያስፈልጋሉ ተብሏል
የአንበጣ መንጋ ክስተት ለተወሰኑ ጊዜያት ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚችል ትንበያዎች አመለከቱ
በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ያጋጠመውን የበርሃ አንበጣን መንጋ ለመከላከል እስከ 10 አውሮፕላኖች እና 150 የመስክ ተሽከርካሪዎች እንደሚያስፈልጉት ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ መንጋውን ለመከላከል የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስቧል፡፡
መንጋው በአሁኑ ወቅት በአፋር፣ በሱማሌ፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ አስተዳደር የተለያዩ ወረዳዎች ተከስቷል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) በሚኒስትሩ የሚመራ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ተባዩን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ርብርርብ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዎች ክልሎችን ተከፋፍለው ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በሰው ሃይል እና በተሽከርካሪ በሚንቀሳቀስ መርጫ መሳሪያ እና አውሮፕላን በመታገዝ የጸረ ተባይ ኬሚካል ርጭት በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ተሽከርካሪን ጨምሮ መንጋውን የመቆጣጠር ጥረቱን ለማገዝ የሚያስችል ድጋፍ በሌሎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እየተደረገ ይገኛልም ብለዋል ዶ/ር ማንደፍሮ፡፡
በቅርቡ ተጨማሪ ስምንት አውሮፕላኖች ከውጭ ገብተዋል፡፡ በመካሄድ ላይ ያለውን ርጭት ለማገዝ የሚያስችል ዝግጅት በማድረግም ላይ ይገኛሉ፡፡
ዶ/ር ማንደፍሮ አሁን ባለው ትንበያ መሰረት የተባዩ ክስተት ለተወሰኑ ጊዜያት ቀጣይነት ሊኖረው ይችላል ብለዋል፡፡
እሱን ለመከላከል 10 አውሮፕላኖች እና 150 የመስክ ተሽከርካሪዎች ያስፈልጋሉ ያሉም ሲሆን አስፈላጊውን ሁሉ ለማሟላት ከተለያዩ ተቋማትና ሀገራት ጋር መንግስት እየተነጋገረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ከአርሶና አርብቶ አደሩ ጀምሮ ሁሉም አካላት መንጋው ወደ ሰብል አምራች አካባቢዎች ተስፋፍቶ የመኸር ሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ርብርብ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አል ዐይን አማርኛ ከሰሞኑ በባለፈው የምርት ዘመን ይጠበቅ ከነበረው ምርት ውስጥ 1 በመቶው ወይም 3.5 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ ምርት በአንበጣ መንጋ ወድሟል ሲል መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡