ጠቅላይ አቃቤ ህግ ባለስልጣናት ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ “የመጨረሻ እድል” ሰጠ
ኮሚሽኑ ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ 184 ከፍተኛ ባለስልጣናትን እንዲከሰሱለት ባለፈው ነሐሴ ጠይቆ ነበር
ጠቅላይ አቃቤ ህግ በመጨረሻው እድል በማይጠቀሙት ባለስልጣናት ላይ ምርመራ እንደሚያደርግ ገለጸ
ጠቅላይ አቃቤ ህግ በመጨረሻው እድል በማይጠቀሙት ባለስልጣናት ላይ ምርመራ እንደሚያደርግ ገለጸ
ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እንዲያስመዘግቡ “የመጨረሻ እድል” መስጠቱን ለፌደራል የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን በደብዳቤ ማሳወቁን የኮሚሽኑ ሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ዳይሬክተር መስፍን በላይነህ ለአል ዐይን ኒውስ ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ ባለፈው ነሀሴ 20 ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ 184 ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በአስገዳጁ አዋጅ መሰረት ስላላስመዘገቡ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ከሶ ተጠያቂ እንዲያደርግለት በደብዳቤ ጠይቆ ነበር፡፡
ዳይሬክተሩ አቶ መስፍን እንደገለጹት ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለኮሚሽኑ በጻፈው ምላሽ “አሁን ባለው ሁኔታ በመንግስት ሹመኞችና ባለስልጣናት ላይ ምርመራ ማካሄድ በመንግስት ስራ“ ላይ ጫና ስለሚፈጥር ባለስልጣናቱ ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል፡፡
ከጥቅምት 2 እስከ 6፣ 2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ባለስልጣናቱ ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ብለዋል አቶ መስፍን፡፡
ጠቅላይ አቃቤ ህግ በተሰጠው የአራት ቀናት ጊዜ ውስጥ ሀብታቸውን በማያስመዘግቡ ባለስልጣናት ላይ ምርመራ እንደሚጀምርና ተጠያቂ እንደሚያጀር ማስታወቁን አቶ መስፍን ገልጸዋል፡፡
ዳሬክተሩ ያላስመዘገቡት ባለስልጣናት እንዳይከሰሱ በ1000 ብር ቅጣት በተሰጠው ቀን ማስመዝገብ ይኖባቸዋል ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ ባለስልጣናቱ ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ለሁለት ጊዜ ቀነ ገደብ አስቀምጦ፣ በሁለቱም ቀነ ገደብ ሀብታቸውን ያለስመዘገቡ ባለስልጣናትን ነበር እንዲከሰሱ ለጠቅላይ አቃቤ ህግ የሰጠው፡፡
የፌደራል መንግስት ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ የሚያስገድደው አዋጅ ቁ.668/2002 ሆኖ በ2002ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ጸድቆ ነበር፡፡ በዚህ አዋድ መሰረት የፌደራል የመንግስት ሰራተኞች፤ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የመንግስት ሰራተኞችንና የህዝብ ተመራጮች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ያስገድዳል፡፡