ኢራን ከሀማስ ጥቃት ጀርባ እጇ እንዳለበት እየተገለጸ ይገኛል
የበርካታ ሀገራት ዜጎች በእስራኤል መገደላቸው ተገለጸ፡፡
በምዕራባዊያን ሀገራት በሽብርተኝነት የተፈረጀው እና በፍልስጤም የሚንቀሳቀሰው ሀማስ ባሳለፍነው ቅዳሜ በእስራኤል ላይ የተቀናጀ ጥቃት መክፈቱ ይታወሳል፡፡
በጥቃቱም እስካሁን ከ700 በላይ ዜጎች በእስራኤል ሲገደሉ ከተገደሉት ውስጥ የውጭ ሀገራት ዜጎችም እንዳሉበት ተገልጿል፡፡
እስራኤል በሀማስ ላይ የመልሶ ማጥቃት የከፈተች ሲሆን ከ300 በላይ ፍልስጤማዊያን መገደላቸውን ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
በርካታ የዓለማችን ሀገራት ስለ እስራኤል-ሀማስ ጦርነት መግለጫ ያወጡ ሲሆን ጉዳዩ ዋነኛ የዓለማችን መነጋገሪያ አጀንዳም ሆኗል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎንም ለጉብኝት እስራኤል የነበሩ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል የተባለ ሲሆን አንዳንድ ሀገራትም የተገደሉ ዜጎቻቸውን ማንነት ይፋ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
የእስራኤል-ሃማስ ጦርነት፤ በጋዛ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
ለአብነትም ታይላንድ 12 ዜጎቿ ተገድለውብኛል ያለች ሲሆን 11 ታግተው ሲወሰዱ ስምንት ዜጎቿ ደግሞ እንደቆሰሉ ገልጻለች፡፡
የአየርላንድ መንግስት በበኩሉ አንድ ዜጋው እስካሁን የት እንዳለ አልታወቀም ያለ ሲሆን አሜሪካ በበኩሏ በርካታ ዜጎቿ ስለመገደላቸው እና ታግተው በሀማስ ታጣቂዎች ስለመወሰዳቸው አስታውቃለች፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በእስራኤል ላይ በተሰነዘረው ጥቃት ከ100 በላይ የሚሆኑ ዜጎቻችን ደህንነት አደጋ ላይ ወድቋል ብለዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ሀማስ በእስራኤል ላይ ካደረሰው የተቀነባበረ ጥቃት ጀርባ ኢራን አጇ እንዳለበት እየተገለጸ ይገኛል፡፡
ዎልስትሪት ጆርናል እንደዘገበው ከሆነ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ሰራዊት ሀማስ እስራኤልን እንዲያጠቃ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ኢራን በበኩሏ የሀማስን ጥቃት እደግፋለሁ ነገር ግን ቀጥታ ድጋፍ ግን አላደረኩም ስትል አስታውቃለች፡፡