የሊባኖሱ ሄዝቦላህ በእስራኤል ላይ የሮኬት ጥቃት መፈጸሙን ገለጸ
“ከፍልስጤማውያን ጋር ተሰልፌያለሁ” ያለው ሄዝቦላህ በአወዛጋቢው የዶቭ ተራራ አካባቢ ሮኬትና ሞርታር መተኮሱን ገልጿል
የሃማስ እና እስራኤል ጦር ግጭት ዛሬም አልበረደም
የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ከጋዘ ሰርጡ ሃማስ ጋር አጋርነቱን አሳይቷል።
ቡድኑ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን በመተኮስ “ከፍልስጤማውያን ጎን ተሰልፌያለሁ” ማለቱንም ታይምስ ኦፍ እስራኤል አስነብቧል።
ሄዝቦላህ ዶቭ ተራራ በተባለው የድንበር ስፍራ በእስራኤል ይዞታዎች ላይ ሮኬቶች እና ሞርታሮች አከታትሎ መተኮሱን ነው ያስታወቀው።
ቡድኑ ጥቃቱ ኢላማውን መምታቱን ቢገልጽም ያደረሰውን ዝርዝር ጉዳት ግን አልጠቀሰም።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ ሄዝቦላህ በሊባኖስ ድንበር አቅራቢያ በፈጸመው የሮኬት ጥቃት የደረሰውን ጉዳት ባይገልጽም የአጻፋ እርምጃ መውሰዱን አብራርቷል።
ሄዝቦላህም እስራኤል በድሮን በፈጸመችው ጥቃት የደረሰውን ጉዳት ከመግለጽ ተቆጥቧል።
ሃማስ በትናንትናው እለት በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል መተኮሱን ተከትሎ ውጥረት ነግሷል።
በሃማስ እና የእስራኤል ጦር ግጭት እስካሁን 256 ፍልስጤማውያን እና 300 እስራኤላውያን ህይወታቸው ማለፉ ነው የተነገረው።
በጋዛ ሰርጥ የሚገኘው የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር እስራኤል በወሰደችው የአጻፋ ምላሽ በጋዛ ብቻ ከ1 ሺህ 700 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጿል።
ሃማስ በርካታ እስራኤላውያንን በምርኮ መያዙን ያስታወቀ ሲሆን፥ የእስራኤል ጦርም የሚወስደውን እርምጃ መቀጠሉን ሬውተርስ ዘግቧል።
የሃማስን ያልተጠበቀ የሮኬት ጥቃት ተከትሎ “ፍልስጤምን ምድረ በዳ ልናደርጋት እንችላለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጋዛ ልዩ የምድር ጦር ዘመቻ ሊከፍቱ እንደሚችሉ ተነግሯል።