የፍልስጤሙ ሃማስ ቡድን እስራኤል ላይ ለምን ጥቃት ከፈተ? ማወቅ ያለብን ነጥቦች
በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት የከፈተው ሃማስ "ለመጨረሻ ጊዜ በቃን ብለን ተነስተናል" ብሏል
የእስራኤል መከላከያ ሚንስቴር ሃማስ “ከባድ ስህተት ሰርቷል፤ የእስራኤል ጦርነቱን ታሸንፋለች” ብሏል
ሃማስ በዛሬው እለት እስራኤል ላይ ድንገተኛ እና ያልተጠበቀ ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ እስራኤል እና ፍልስጤም ወደ አዲስ ጦርነት የማምራታቸው ነገር እውን እየሆነ መጥቷል።
ሃማስ ከጋዛ ሰርጥ በተለያዩ አቅጣጫዎች እስራኤል ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት የከፈተ ሲሆን፤ እስራኤል ደግሞ በአጸፋው በርካታ የአየር ድብደባዎችን እየፈጸመች ትገኛለች።
የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሃማስ “ ዘመቻ አል አቅሳ ጎርፍ” የሚል መጠሪያ የተሰጠው ጥቃት በእስራኤል ላይ የከፈተ ሲሆን፤ ይህም ከፈረንጆቹ 2021 ወዲህ በግዙፍነቱ የመጀመሪያው ነው።
ሃማስ ወደ እስራኤል 5 ሺህ ሮኬቶችን መተኮሱን የገለፀ ሲሆን፤ እስራኤልም የሃማስ ቡድን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው መግባታቸውን አረጋግጣለች።
ሃማስ ሮኬቶቹን ከንጋቱ 12፤30 ጀምሮ መተኮስ የጀመሩ ሲሆን፤ ሃማስ ሮኬቶቹም ወደ ሩቅ ምስራቅ ቴል አቪቭ ተኩሷል፤ በደቡብ በኩል ደግሞ ታጣቂዎቹን ወደ እስራኤል አስገብቷል።
የእስራኤል አየር ኃይልም በርካታ የጦር ጄቶችን በማሰማራት በጋዛ ሰርጥ ውስጥ በሚገኙ የሃማስ ኢላማዎችን ሲደበድብ ውሏል።
በደቡባዊ እስራኤል በተለያዩ ቦታዎች በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል የመሳሪያ ተኩስ ፍልሚያ አሁንም መቀጠሉን የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ሃማስ ቡድን እስራኤል ላይ ለምን ጥቃት ከፈተ?
የሃማስ መሪ መሐመድ ዴፍ "ለመጨረሻ ጊዜ በቃን ብለን ተነስተናል" ሲል ተናግሯል።
የሃማስ ቃል አቀባይካሊድ ካዶሚ በበኩሉ፤ ቡድኑ በእስራኤል ላይ የጀመረው ወታደራዊ ዘመቻ ባለፉት አስርት ዓመታት ፍልስጤማውያን ላይ ለተፈጸመው ግፍ ምላሽ ነው ብሏል።
“ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በጋዛ የሚፈጸመውን ግፍ እንዲያስቆም እንፈልጋለን” ያለው ቃል አቀባዩ፤ “አል ኣቀሳን ጨምሮ ቅዱሳን ስፍራዎቻችን ለዘመቻው መጀመር መነሻ ነው” ብሏል።
መሳሪያ የታጠቀ ማንኛውም ፍልስጤማዊ ጦርነቱን እንዲቀላቀል ጥሪ ያቀረበው ሃማስ፤ የዌስት ባንክ ታጣቂዎች፣ የአረብ ማህበረሰብ እና ሙስሊም ሀገራት ዘመቻውን እንዲቀላቀሉ በቴሌግራም በለቀቀው መግለጫ ጥሪ አቅርቧል።
የእስራኤል መንግስት ስለ ጥቃቱ ምን አለ?
የእስራኤል ጦር ጋዛ አቅራቢያ የሚኖሩ እስራኤላውያን ከቤታቸው እንዳይወጡ እና ምሽግ ውስጥ እንዲሸሸጉ አሳስቧል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሀገራቸው ጦርነት ውስጥ መሆኗን ጠቅሰው፤ ጦርነቱን ግን ታሸንፋለች ብለዋል።
የእስራኤል መከላከያ ሚንስትር ዮአቭ ጋላንት ሃማስ “ከባድ ስህተት ሰርቷል” ሲሉ “የእስራኤል መንግስት በዚህ ጦርነት እንደሚያሸንፍ አስታውቀዋል።