የውጭ ሀገር ሰላም አስከባሪዎችን በዩክሬን የማሰማራቱ ጉዳይ በብራሰልስ ይመከርበታል -ዜለንስኪ
የጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ፖላንድ እና የኔቶ መሪዎች ዛሬ በቤልጂየም ለኬቭ በሚደረግ ድጋፍ ዙሪያ ይመክራሉ
በፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የቀረበው ሃሳብ በአውሮፓ መሪዎች ዘንድ እስካሁን ስምምነት አልተደረሰበትም
በዩክሬን የውጭ ሀገር ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን የማሰማራቱ ጉዳይ በብራሰልስ በሚደረገው ምክክር እንደሚመከርበት ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ተናገሩ።
የጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ፖላንድ እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች እንዲሁም የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ለኬቭ ተጨማሪ ድጋፍ በሚደረግበት መንገድ ዙሪያ ዛሬ በቤልጂየም መዲና ይገናኛሉ።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ኬቭ የኔቶ አባል እስክትሆን ድረስ የውጭ ሀገራት ወታደሮች ገብተው እንዲያግዟት ከ11 ቀናት በፊት ከጀርመን ባለስልጣናት ጋር ሲመክሩ ሃሳብ አቅርበዋል።
የውጭ ሀገራት ወታደሮችን ወደ ዩክሬን የመላኩን ሃሳብ አስቀድመው ያቀረቡት ግን የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ናቸው።
ማክሮን በያካቲት ወር 2024 ያቀረቡት ሃሳብ ግን እስካሁን በሌሎች የአውሮፓ መሪዎች ድጋፍ አልተቸረውም።
የፖላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ ወደ ዩክሬን ወታደሮችን የመላክ ሃሳብ የለንም፤ የኬቭን የኔቶ አባልነት እውን ለማድረግ ግን የትኛውንም ድጋፍ እናደርጋለን ማለታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ዩክሬን እና አጋሮቿ ሰሜን ኮሪያ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ለሩሲያ በመላክ ከዩክሬን ጦር ጋር መዋጋት መጀመራቸውን ይገልጻሉ።
ፒዮንግያንም ሆነች ሞስኮ የወታደሮቹን መግባት በተመለከተ በግልጽ ባይናገሩም የኪም ጆንግ ኡን ሀገር ፑቲንን ለድል ለማብቃት ድጋፌ ይቀጥላል ብላለች።
ኬቭ በብራሰልሱ ስብሰባ ይሄንኑ ጉዳይ በማንሳት የሩሲያን ግስጋሴ የሚያስቆም ድጋፍ ታገኝ ዘንድ ከአውሮፓ መሪዎች ጋር ትመክራለች ተብሏል።
በተለይም የረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች እና የውጊያ ጄቶች ድጋፍ እንዲደረግላትና በሚሳኤሎቹ ሩሲያን ዘልቃ ለመምታት የተሰጣት ፈቃድ እንዲጠናከር ታግባባለች ብለዋል ዜለንስኪ።
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ድርድር ከመጀመሯ በፊት በአውደ ውጊያውም ሆነ በዲፕሎማሲው አሁን ካለችበት በተሻለ ቁመና እንድትቀርብ በብራሰልስ ከአጋሮቿን ከፍተኛ ድጋፍ ትጠብቃለች።
ከአንድ ወር በኋላ ወደ ዋይትሃውስ በድጋሚ የሚዘልቁት ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሶስት አመት ሊደፍን ሁለት ወራት የቀረውን የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት አስቆማለሁ ብለዋል።
ዜለንስኪ ለድርድር ዝግጁ እንዲሆኑ የጠየቁ ሲሆን፥ የሩሲያ እና ዩክሬን ልዩ መልዕክተኛቸውን በቅርቡ ወደ ኬቭ እንደሚልኩም አስታውቀዋል።
ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸውና ድርድሩ ከመጀመሩ በፊት ኬቭ በሞስኮ የተነጠቀችውን መሬት በጥቂቱም ቢሆን ለማስመለስ ከፍተኛ ወታደራዊ ድጋፍ ያስፈልጋታል።
ተንታኞች ግን ለሶስት አመት ከምዕራባውያን በ100 ቢሊየን ዶላር የሚቆጠር ድጋፍ ተደርጎላት ከ20 በመቶ በላይ መሬቷን ከሩሲያ ያላስለቀቀችው ሀገር ድርድር ብቸኛ አማራጯ ነው ይላሉ።