ፑቲን "ምዕራባውያን የሩሲያን ትዕግስት እየተፈታተኑ ወደ ቀይ መስመሯ እየገፋፏት ነው" አሉ
ሞስኮ ማንንም እንደማትታገስና እርምጃ ለመውሰድ እንደምትገደድ ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል
ፑቲን በዩክሬን የሚገኙ የሩስያ ሃይሎች በ2024 እስካሁን 189 ሰፍራዎችን መቆጣጠራቸውን ተናግረዋል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን "ምእራባውያን የሞስኮን ትዕግስት እየተፈታተኑ ወደ ቀይ መስመሯ እየገፋፏት ነው" ሲሉ ከሰሱ።
ፑቲን ከሩሲያ መከላከያ አመራሮች ጋር ሲመክሩ ባደረጉት ንግግር ሩሲያ ማንንም እንደማትታገስና እርምጃ ለመውሰድ እንደምትገደድ ተናግረዋል።
ፑቲን አክለውም ሩሲያ የአሜሪካን እንቀስቃሴ እንዲሁም በዩክሬን የአጭር እና መካከለኛ ርቀት ሚሳኤሎችን ለማስቀመጥ የምታደረጋቸውን ተግባራት በከፍተኛ ትኩረት እየተከታተለች ነው ብለዋል።
አሜሪካ የረጅም እና መካከለኛ ርቀት ሚሳኤሎችን ማሰማራቷን ካላቆመች ሩሲያ በራሷ ፈቃድ ተመሳሳይ ሚሳኤሎቿ ላይ ያስቀመጠችውን ገደብ በማንሳት እንደምታሰማራም ነው ያስጠነቀቁት።
የሩሲያ የኒዩክሌር የጦር መሳሪያዎች ሁልጊዜም ለመከላከል መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
ፕሬዝዳንቱ በዩክሬን የሚገኘው የሩሲያ ጦር በርካታ ቦታዎችን እየተቆጣጠረ ወደፊት መገስገሱን እንደቀጠለ ገልጸዋል።
እየተገባደደ ባለው የፈረንጆቹ 2024 ዓመት ብቻ በዩክሬን ውስጥ የሚገኘው የሩሲያ ጦር 189 ሰፍራዎችን መቆጣጠሩን አስታውቀዋል።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ያሳለፍነው ህዳር ወር ግጭቱ ወደ ከፍተኛ ሁኔታ የተሻገረበት ነበር።
ጦርነቱ እንደ አዲስ ያገረሸው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዩክሬን የአሜሪካ የረጅም ርቀት ሚሳዔሎችን ተጠቅማ የሩሲያ ግዛት ውስጥ ጥቃት እንደትፈጽም መፍቀዳቸውን ተከትሎ ነው።
ሞስኮ ዩክሬንን "ኦርሼኒክ" በተባለ አዲስ የመካከለኛ ርቀት ባለስቲክ መሳሪያ ስትመታ የአለም አቀፉን ማህበረሰብ አስደንግጦ ተጨማሪ ስጋትን ከፍ በማድረግ የሩሲያ ዩክሬን የሚሳኤል ፍጥጫን ትንሽ ረገብ አድርጎታል።
ይሁን እንጂ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር የገጠመችው ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ፈጣን የተባለውን ግስጋሴ እያደረገች የዩክሬንን ግዛቶች እየተቆጣጠረች መሆኑን የዘርፉ ተንታኞች ይናገራሉ።
የሩሲያ ጦር ባሳለፍነው ሳምንት ብቻ 235 ካሬ ኪ.ሜ የዩክሬንን መሬት ተቆጣጥሯል የተባለ ሲሆን፤ ይህም የፈረንጆቹ 2024 አዲስ ክብረወሰን ነው።
ሩሲያ እየተገባደደ ባለው የፈረንጆቹ ህዳር ወር ብቻ 600 ካሬ ኪ.ሜ የዩክሬንን መሬት መቆጣጠሯንም ዲፕ ስቴት የተባለውን እና ለዩክሬን ጦር ቅርበት ያለውን ተቋም ዋቢ በማድረግ የወጣ መረጃ ያመለክታል።