ሀይለማሪያም ደሳለኝን ጨምሮ ሶስት የቀድሞ መሪዎች የኮንጎን የሰላም ንግግር እንዲመሩ ተመደቡ
የቀድሞ መሪዎቹ ዴሞክራቲክ ኮንጎን እና የኤም 23 አማጺያንን ለማሸማገል የተሾሙት በቀጠናዊ የባለብዙ ወገን ድርጅቶች ነው

የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡህሩ ኬንያታ እና የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዝደንት ኦባሳንጆ የፕሪቶሪያው ስምምነት ዋና አደራዳሪዎች እንደነበሩ ይታወሳል
የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ፣ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡህሩ ኬንያታ እና የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ በዴሞክራክ ኮንጎ እና በኤም 23 አማጽያን መካከል ሰላም እንዲፈጠር አሸማጋይ ሆነው ተመድበዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካ ልማት ማህበረሰብ (ኤስኤዲሲ) እና የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ (ኢኤሲ) የቀድሞ መሪዎቹ በምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ቀጠናዊ የሰላም ሂደት አስተባባሪ ሆነው እንዲሰሩ ሾመዋል፡፡
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የኢኤሲ እና የኤስኤዲሲ ሀገራት መሪዎች በታንዛኒያ ዳሬሰላም የተካሄደውን የመሪዎች ጉባኤ ተከትሎ በምስራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያለውን ግጭት ለመፍታት ነው የቀድሞ መሪዎቹ ሀላፊነት የተሰጣቸው፡፡
ከታህሳስ ወር ጀምሮ ውጊያቸውን እያጠናከሩ የሚገኙት አማፅያን ጎማ እና ቡካቩን የመሳሰሉ ቁልፍ የኮንጎ ስፍራዎችን መቆጣጠር ችለዋል፡፡
የኮንጎዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁዲት ሱሚንዋ ቱሉካ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ባደረጉት ሪፖርት በዚህ አመት ብቻ በግጭቱ ከ7 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸውን ገልጸዋል።
የተሾሙት አስተባባሪዎች በኮንጎ መንግስት፣ በታጣቂ ቡድኖች እና በቀጠናዊ ባለድርሻ አካላት መካከል መረጋጋትን ለመፍጠር እና ግጭቱ እንዳይባባስ ለመከላከል ከፍተኛ ደረጃ ያለው ድርድር ይመራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ጦርነቱን ለማስቆም የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ከሶስት ቀናት በኋላ በሚደረገው የጋራ የሚኒስትሮች ስብሰባ የሚቀጥል ሲሆን የተኩስ አቁም ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዙ የስምምነት ሰነዶች ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተለይም ግጭት ባለበት ምስራቃዊ አካባቢ ያለውን ቀውስ ለማርገብ የደቡብ አፍሪካ ልማት ማህበረሰብ (ኤስኤዲሲ) እና የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ (ኢኤሲ) ሁሉን ያሳተፈ አካሄድ ተግባራዊ እንዲሆን ወስነዋል፡፡
በቅርቡ በታንዛኒያ የተካሄደው የጋራ ጉባኤ የቀጠናዊ ባለብዙ ወገን ድርጅቶች አባል ሀገራት ሚኒስትሮች በዲአርሲ የጸጥታ ሁኔታ ላይ ያቀረቡትን የጋራ ስብሰባ ሪፖርት የገመገመ ሲሆን ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ተሳትፎ ለግጭቱ ዘላቂ መፍትሄ ሆኖ እንዲቀጥል አጽንኦት ሰጥቷል።
እነዚህን ጥረቶች ለማጠናከር የጉባኤው ሊቀመንበሮች ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመመካከር የሰላም ሂደቱን የሚደግፉ ሌሎች የአፍሪካ ቀጠና ተወካዮች በተጨማሪ አመቻችነት እንዲሾሙ አዟል።
የጋራ ጉባኤው ከመንግስት የፖለቲካ እና ወታደራዊ አመራሮች እንዲሁም ከኤም 23 አማጺያን መሪዎች በተጨማሪም ከሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ጋር ቀጥተኛ ድርድር እና ውይይት እንዲቀጥል መመሪያ አስተላልፏል።